በሊጉ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ መድን የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሊጉ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ መድን የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 7/ 2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት ተስተካካይ መርሃ ግብር ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ መድን ዛሬ ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።
የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከቀኑ 9 ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም ይካሄዳል።
በአዲስ አበባ ስታዲየም የ16 ጊዜ የሊጉ አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና የወቅቱ የሊጉ ዋንጫ ባለቤት ኢትዮጵያ መድን የሚያደርጉት ጨዋታ የተመልካቾችን ትኩረት ስቧል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ በሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች ሶስት ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ሽንፈትን አስተናግዷል። በጨዋታዎቹ አምስት ግቦችን ሲያስቆጥር ሁለት ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፏል።
ቡዱኑ በዘጠኝ ነጥብ ስድስተኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው ኢትዮጵያ መድን በበኩሉ በውድድር ዓመቱ ባደረጋቸው ሶስት ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ድል ሲቀናው ሁለት ጊዜ አቻ ተለያይቷል። ሁለት ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ አንድ ግብ ተቀጥሮበታል።
መድን በአምስት ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ጨዋታው ተመጣጣኝ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።
ሁለቱ ቡድኖች በ2017 ዓ.ም በሊጉ ያደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች በተመሳሳይ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል።
የቡድኖች ጨዋታ ኢትዮጵያ መድን በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ከግብጹ ፒራሚድስ ጋር በነበረው የሁለተኛ ዙር ማጣሪያ ምክንያት የተራዘመ ነው።
ኢትዮጵያ መድን በቀጣይ በሚገለጽ ቀን እና ቦታ ከሸገር ከተማ ጋር ቀሪውን ተስተካካይ ጨዋታ እንደሚያደርግ የሊጉ አክሲዮን ማህበር አስታውቋል።