ቀጥታ፡

የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በተሰሩ ስራዎች በግብርናው ዘርፍ እድገት ተመዝግቧል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 7/2018(ኢዜአ)፦ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በተሰሩ ስራዎች በግብርናው ዘርፍ እድገት ማስመዝገብ መቻሉን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ሃላፊ አበራ ወንድሙ ገለጹ።

በዞኑ በተያዘው የምርት ዘመን ከ150 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በተለያዩ የመኸር ሰብሎች ማልማት መቻሉንም አስታውቀዋል፡፡

20ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓልን ምክንያት በማድረግ ከሀገሪቱ የተወጣጡ የጋዜጠኞች ቡድን አካባቢውን ጎብኝቷል፡፡

በዚሁ ወቅት የዞኑ አስተዳደር በሰጠው ማብራሪያ የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ አርሶ አደሩ የምግብ ዋስትናውን እንዲያረጋግጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡


 

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ሃላፊ አበራ ወንድሙ፥ እንደ ሀገር ከተረጅነት ለመውጣት የሚደረገውን እንቅስቃሴ ስኬታማ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በዚህም ከዚህ በፊት በእርሻ ስራ የማይታወቁ አካባቢዎችን ወደ ስራ ማስገባት መቻን ጠቅሰዋል፡፡

በተጨማሪም የአፈር አሲዳማነት ችግርን ለመከላከል ከ30 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማከሚያ ኖራ ጥቅም ላይ መዋሉን ገልጸዋል፡፡

የበቆሎ ምርትና ምርትማነትን ለማሳደግ በሞዴል አርሶ አደሮች ደረጃ በክላስተር በተሰራው ስራ ከፍተኛ ምርት መገኘቱን አስታውቀዋል።

ይህንኑ ምርታማነት በሁሉም አካባቢዎች በማስፋት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

ከዚህ በፊት ባልተለመደ መልኩ በአርሶ አደር ደረጃ ለወጪ ንግድ የሚሆኑ እንደ ሩዝ እና ሮዝመሪ ያሉ የግብርና ምርቶችን የማስፋት ስራ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።


 

በአዲስ እይታ እየተካሄደ ያለው የሌማት ትሩፋት ንቅናቄ የወተት፣ የዶሮና ማር ሞዴል መንደሮችን ለመፍጠር ማስቻሉን ሃላፊው ተናግረዋል።

በዞኑ በራስ አቅም ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን የመቋቋም አቅም ለመፍጠር የተጀመረው ጥረት በአጭር ጊዜ አበረታች ውጤት ማስገኘቱን አስረድተዋል።

ለአብነትም በጉመር ወረዳ እንደ ዞን በዚህ ዓመት ለአደጋ ጊዜ ምላሽ የሚሆን ከ16 ሺህ 500 ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም