ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በቀጣናው ደህንነት እና ልማት ያላትን ሚና አውስትራሊያ ትደግፋለች- አምባሳደር ፒተር ሃንተር

አዲስ አበባ፤ ህዳር 7/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በቀጣናው ደህንነት እና ልማት ውስጥ እየተወጣች ያለውን ትርጉም ያለው ሚና አውስትራሊያ እንደምትደግፍ አምባሳደር ፒተር ሃንተር (ዶ/ር) ገለጹ።

አውስትራሊያ ከኢትዮጵያ ጋር በአዳዲስ መስኮች ትብብር የመፍጠር ፍላጎት አላት ብለዋል።

በኢትዮጵያ የአውስትራሊያ አምባሳደር ፒተር ሃንተር (ዶ/ር) የአፍሪካ ቀንድ ውስብስብ ፈተናዎች ያሉበት ቀጣና እንደሆነ ገልጸዋል።

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ በቀጣናው ደህንነት እና ልማት እያደረገች ያለውን ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ እንደምትደግፍም አመልክተዋል።

አምባሳደር ሃንተር አውስትራሊያ እና ኢትዮጵያ ያላቸው የሁለትዮሽ የትብብር አድማስ እየሰፋ እንደሚገኝ አንስተዋል።

የህዝብ ለህዝብ ትስስር፣ ንግድ፣ ኢንቨስትመንት እና ትምህርትን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

የአውስትራሊያ  መንግስት ከኢትዮጵያ ህዝብ እና መንግስት ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ለማጠናከር በቅርበት እየሰራ ይገኛል ነው ያሉት።

አምባሳደሩ ኢትዮጵያ እየተገበረች ያለችውን የኢኮኖሚ ሪፎርሞች ያደነቁ ሲሆን ሪፎርሙ የባለሀብቶችን የራስ መተማመን መጨመሩንና አዳዲስ እድሎችን መፍጠሩን አብራርተዋል።

አውስትራሊያ ከኢትዮጵያ ጋር በቱሪዝም፣ ማዕድን እና ግብርና ዘርፍ ያላትን ትብብር የማጠናከር ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል።

በተጨማሪም አምባሳደሩ ለአዲስ አበባ ለውጥ ያላቸውን አድናቆት ገልጸው ይህም የኢትዮጵያን እድገት ምልክት ነው ብለዋል።

ከዓለም አቀፍ ጉዳዮች ጋር በተገናኘም አውስትራሊያ የባለብዙወገን መድረክ ማሻሻያ እንዲደረግ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግና አፍሪካ በዓለም የወሳኔ ሰጪነት ውስጥ ያላት ሚና ማደግ እንደሚገባው አመልክተዋል።

አውስትራሊያ ደህንነት እና ልማትን ጨምሮ ከአፍሪካ ጋር ያላትን ትብብር ለማጠናከር እንደምትሻም አክለዋል

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም