የከሚሴ እና የወሎ ሕዝብ ሰላምንና አብሮነትን በማስቀደም ለብልጽግና የምታደርጉትን ርብርብ ማስቀጠል አለባችሁ - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የከሚሴ እና የወሎ ሕዝብ ሰላምንና አብሮነትን በማስቀደም ለብልጽግና የምታደርጉትን ርብርብ ማስቀጠል አለባችሁ - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ህዳር 6/2018(ኢዜአ)፦ የከሚሴ እና የወሎ ሕዝብ ሰላምንና አብሮነትን በማስቀደም ለብልጽግና የምታደርጉትን ርብርብ ማስቀጠል አለባችሁ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ በከሚሴ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፤ የወሎን የመሰለ የልብ ፍቅር ካለ ክፋት እና ጥላቻ መቼም እንደማያሸንፉ ገልጸዋል፡፡
የልብ ፍቅር ምን እንደሆነ ለሚያውቀው እና ፍቅርን በተግባር እየኖረ ላለው ለከሚሴ እና ለወሎ ሕዝብ መንገር አይጠበቅብንም ሲሉም ተናግረዋል።
ከወሎ ሕዝብ የሚመነጭ ፍቅር እንኳን ለወሎ ለመላው ኢትዮጵያም የሚተርፍ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
የከሚሴ እና የወሎ ሕዝብ እንደሚያውቀው ሰላም ከእውነተኛ ልብ ይመነጫል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዚህም ለሌላውም የሚተርፍ ፍቅር እንዳለው ጠቅስዋል፡፡
የከሚሴ ሕዝብ በፍቅር እና በጠንካራ ሠራተኛነቱ የሚታወቅ ህዝብ መሆኑንም ተናግረዋል።
ፍቅር ከልብ እንደሚመነጨው ሁሉ ሰላምም ከውስጥ ይመነጫል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ውስጡ ሰላም የሌለው ከውጪ ለመግዛት ቢሞክር እንደማይችል ገልጽዋል።
በመሆኑም ሰላም ሁልግዜም ከውስጥ መጥፋት የሌለበትና ለሌሎችም የምታስተምሩት መሆን አለበት ብለዋል።
ከዚህ በፊት በአንድነት አስቸጋር የነበሩ ግዚያትን አሳልፋችኋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከአሁን በኋላ ግን ቀጣዩ ትውልድ የተሻለ ኑሮ እንዲኖር በጋራ እንሰራለን ነው ያሉት።