ቀጥታ፡

የመደመር መንግሥት የከተሞችን እድገት ለማረጋገጥ ተገቢ አቅጣጫ አመላክቷል - ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 6/2018(ኢዜአ)፦ የመደመር መንግሥት የከተሞችን እድገት ለማረጋገጥ ተገቢ አቅጣጫ በግልጽ ማመላከቱን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ገለጹ።

10ኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም "የከተሞች ዕድገት ለኢትዮጵያ ልህቀት” በሚል መሪ ሀሳብ በአፋር ክልል ሰመራ ሎጊያ ከተማ መካሄድ ጀምሯል፡፡

ዛሬ "የመደመር መንግሥት እና የኢትዮጵያ ክትመት" በሚል የፓናል ውይይት ተካሂዷል።


 

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በዚሁ ወቅት፤ የመደመር መንግሥት የከተሞችን እድገት ለማረጋገጥ ተገቢ አቅጣጫ በግልጽ ያመላከተ መሆኑን ተናግረዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የተጀመረው የኮሪደር ልማት በ73 ከተሞች ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቁመዋል።

የኮሪደር ልማቱ ብዙ ድል የተገኘበት ሰው ተኮር ስራ መሆኑን ጠቁመው፤ የከተሞችን ገጽታ በከፍተኛ ሁኔታ መቀየሩን አንስተዋል።

የለውጡ መንግስት በክትመት ስራዎች ላይ የነበሩ ስብራቶችን በመጠገን ምርጥ ከተሞች እየተፈጠሩ እንደሚገኝም ገልጸዋል።


 

ከተሞች በራስ አቅም ለመልማት እያከናወኑት ያለው ስራ የሚበረታታ መሆኑንም ተናግረዋል።

በቀጣይም ሚኒስቴሩ የከተማ አመራር አባላት የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር አለማየሁ አየለ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ያሉ ከተሞች ከእድሜያቸው አኳያ ሲታዩ አለማደጋቸውን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት እነዚህን ከተሞች የማዘመን ስራዎች በትኩረት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸው፤ እነዚህን ስራዎች ዘላቂ ለማድረግ ብዙ መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ከዚህ አኳያ የመደመር መንግሥት ተወዳዳሪ ከተሞችን ለመፍጠር የሚያስችሉ መንገዶችን ያሳየ መሆኑን አመልክተው፤ ከተሞችን በማዘመንበኩል የኮሪደር ልማት ፈር ቀዳጅ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በኢትዮጵያ ክትመት ተስፋም እድልም ነው ያሉት ደግሞ ከዩኤን ሀቢታት የመጡት አበበ ዘልኡል ናቸው።

ከክትመት በፊት የመሰረተ ልማት ስራዎች መቅደም እንዳለባቸው ጠቁመው፤ ለዚህም ውጤታማ እቅድ ማውጣት እና ይህንንም በተቀናጀ አግባብ መምራት እንደሚገባ አመልክተዋል።

በተጨማሪም የካዳስተር ስርዓት ማዘመን እንደሚገባ ገልጸው፤ ይህም ሀብትን በአግባቡ ለመምራትና ለማግኘት ያስችላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም