ኢትዮጵያ (ኮፕ 32)ን እንድታስተናግድ መመረጧ ለአየር ንብረት ለውጥ እርምጃ ላላት ጽኑ ቁርጠኝነት እውቅና የሰጠ ነው - ኢጋድ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ (ኮፕ 32)ን እንድታስተናግድ መመረጧ ለአየር ንብረት ለውጥ እርምጃ ላላት ጽኑ ቁርጠኝነት እውቅና የሰጠ ነው - ኢጋድ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 6/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ 32ኛውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ጉባኤ(ኮፕ 32)ን እንድታስተናግድ መመረጧ ለአየር ንብረት ለውጥ እርምጃና አረንጓዴ ልማት ቁርጠኝነቷ እውቅና የሰጠ መሆኑን የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) ገለጸ።
የድርጅቱ ዋና ጸሀፊ ወርቅነህ ገበየሁ(ዶ/ር) ኢትዮጵያ ኮፕ 32 እንድታዘጋጅ መመረጧን ተከትሎ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ጉባኤውን ማዘጋጀቷ በአየር ንብረት እና ልማት ያላት መሪነት እያደገ መምጣቱን የሚያሳይ ነው ብለዋል።
የአካባቢ ስነ ምህዳርን ወደ ነበረበት የመመለስ፣ ዘላቂ እድገትና የማይበገር አቅም ለመገንባት ያላትን ጠንካራ ቁርጠኝነት የሚያመላክትና ለዚህም ስራዋ እውቅና የሰጠ መሆኑን አመልክተዋል።
አረንጓዴ ዐሻራ እና የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ አረንጓዴ ልማት ስራ ማሳያዎች እንደሆኑም ነው የተናገሩት።
ኮፕ 32 ለኢጋድ ቀጣና ወሳኝ መድረክ መሆኑን ገልጸው ተቋሙ ድርቅ፣ የአየር ንብረት ለውጥ የፈጠረው የዜጎች መፈናቀልና የውሃ እጥረትን ጨምሮ ሌሎች አንገብጋቢ አጀንዳዎች የበለጠ ትኩረት እንዲሰጣቸው እንደሚያደርግ አመልክተዋል።
ኢጋድ ከኢትዮጵያ፣ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ማዕቀፍ ጽህፈት ቤት(UNFCCC Secretariat) እና ዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር በመሆን ጉባኤው ሁሉን አሳታፊ፣ የአፍሪካ የቅድሚያ ትኩረቶች ማዕከል ያደረገና ለአየር ንብረት ለውጥ ዘላቂ መፍትሄ የሚገኝበት እንዲሆን በትብብር እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።
በብራዚል ቤለም እየተካሄደ የሚገኘው 30ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ጉባኤ(ኮፕ 30) ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2027 የሚካሄደውን ኮፕ 32 ጉባኤ እንድታስተናግድ መመረጧ ይታወቃል።
የአፍሪካ ሀገራት ለኢትዮጵያ የኮፕ 32 የማስተናገድ ፍላጎት ሙሉ ይሁንታቸውን ሰጥተዋል።