ቀጥታ፡

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ህዝቡ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያለውን ቅሬታ በዘላቂነት ይፈታል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 6/2018(ኢዜአ)፦ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ህዝቡ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያለውን ቅሬታ በዘላቂነት እንደሚፈታ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የደሴ ከተማን መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት አስጀምረዋል፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፤ ደሴ ከተማ በሀገረ መንግሥት ግንባታ ዘመን ተሻጋሪ ገድል የጻፈች፣ የሰለጠነ ማህበረሰብ የገነባች፣ የዘመናዊ መገለጫ ከተማ መሆኗን ገልጸዋል፡፡

ህዝቡ አስተዋይ፣ ለፍትህ የቆመ፣ በውይይት የሚያምን፣ የሰላም አምባሳደር የልማት አርበኛ በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የወሎ ምድር ለኢትዮጵያዊነት የመደመር ቅኝት ማሳያ፣ ድንቅ እሴት እንደ ቦርከና ወንዝ ሞልቶ የሚፈስበት የአብሮነት እና የመዋደድ ተምሳሌት መሆኑንም አንስተዋል፡፡

ወሎ የጥበብ መፍለቂያና የዕውቀት ማዕድ መሆኗን የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የወሎዋ ዕምብርት ደሴ ከተማ አሁን በከፍተኛ የልማተ እንቅስቃሴ ላይ ትገኛለች ብለዋል፡፡

የደሴ ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት በከተማዋ የተጀመረውን የልማት ጉዞ ለማሳለጥ የጎላ አበርክቶ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢኒሼቲቭ የሆነው መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት በተለያዩ አካባቢዎች በማንዋል ሲሰጥ የቆየውን የመንግሥት አገልግሎት በአንድ ማዕከል ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

በመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት የተገልጋዮችን ጊዜና ጉልበት በመቆጠብ በህዝብና መንግሥት መካከል ያለውን ጥብቅ ቁርኝት ወደ ተሻለ ደረጃ እንደሚያሳድግ ገልጸዋል፡፡

ብልሹ አሰራርን በማስወገድ ዘመኑን የዋጀና ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት መስጠት እንደሚያስችል ገልጸው፤ በደሴ ከተማ የተሰራው ማዕከል የህዝቡን የረጅም ጊዜ የፈጣን አገልግሎት ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በለውጡ መንግሥት ደሴ የብልፅግና ብርሃን ወጋገን ፈንጥቃለች፣ ለኗሪዎቿ ምቹ የበለፀገች እና የተዋበች ከተማ መሆን የሚያስችላትን የተስፋ ጎዳና ጀምራለች ብለዋል፡፡

የመጀመሪያው ምዕራፍ የደሴ የኮሪደር ልማት የከተማዋን ውበት እየገለጠ መሆኑን በመጥቀስ፤ ለተሻለ አፈጻጸም ህዝቡና አመራሩ ተጋግዞ መስራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ሰላምና ልማት ተመጋጋቢ መሆናቸውን የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የተጀመረው ልማት ከግብ እንዲደርስ ህዝቡ የሰላም ዘብነቱን አጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም