ቀጥታ፡

የሌማት ትሩፋት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታችንን እያሳደገ ነው  -  በይርጋለም ከተማ ነዋሪዎች 

ሀዋሳ፤ ህዳር 6/2018(ኢዜአ)፡- የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ተጠቅመው በእንስሳት እርባታ ላይ በመሰማራት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን እያሳደጉ መሆኑን በሲዳማ ክልል ይርጋለም ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

የሌማት ትሩፋት በምግብ ራስን በመቻል የዜጎችን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ የሚያስችልና በእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ምርትና ምርታማነት ላይ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት እንዲቻል የተቀረጸ ፕሮግራም ነው፡፡


 

በዋናነትም እንቁላል፣ ዶሮ፣ ማር፣ ወተትና ዓሳ ልዩ ትኩረት የተሰጣቸው መስኮች ሲሆኑ መርሃ ግብሩ ከተጀመረ ወዲህ እጅግ በርካታ ለውጦች ተመዝግበዋል።

በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የወተት፣ የእንቁላል፣ የማርና የአሳ አርባታ ማዕከላትን ከመገንባት ጀምሮ በግል ቢያንስ በዶሮ እርባታ በመሳተፍ በምግብ ራስን ከመቻል ባለፈ ለገበያ በማቅረብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እንዲያድግ ምክንያት ሆኗል፡፡


 

በመርሃ ግብሩ የሲዳማ ክልል በሰባት ፓኬጆች መንደር በማደራጀት ውጤት እያስመዘገበ ሲሆን በወተት ልማት ከሚገኘው ክልላዊ ምርት ውስጥ በቀን እስከ 4ሺህ 500 ሊትር ወተት ለአዲስ አበባ ገበያና ለይርጋለም ማቀነባበሪያዎች እያቀረበ ይገኛል።

በክልሉ በመስኩ ተሰማርተው የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ማሳደግ የቻሉ የይርጋዓለም ከተማ ነዋሪዎች ለኢዜአ እንደገለጹት የመርሃ ግብሩ መጀመር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን እንዲያሳድጉ አድርጓል፡፡


 

በከተማው በወተት ልማት የተሰማሩት ደረጀ ኢጃሞ በአንዲት የወተት ላም ስራ መጀመራቸውን ጠቅሰው የከብቶቹን ቁጥር 30 በማድረስ በቀን ከ140 ሊትር በላይ ወተት ለአካባቢው ገበያ እያቀረቡ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡

በሚያገኙት ገቢም በስራቸው የሥራ ዕድል ለፈጠሩላቸው 13 ሰዎች በወር እስከ 60 ሺህ ብር እንደሚከፍሉ ነው የገለፁት፡፡


 

በከተማው የዛሬ ዓመት ገደማ ሥራውን የጀመረው ጋኔ የዶሮ እርባታ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ወጣት ኢየሩሳሌም አለማየሁ አምስት ሺህ የዶሮ ጫጩቶችን በማስገባት ስራ መጀመሯን ተናግራለች፡፡

ድርጅቱ አሁን ላይ በቀን 3ሺህ 500 እንቁላል በመሰብሰብ ለነጋዴዎች እንደሚያስረክብ ገልፃ አዋጭነቱን በመመልከት ተጨማሪ ሰባት ሺህ ጫጩቶችን ማስገባቷን ገልፃለች፡፡


 

የይርጋለም ከተማ የእንስሳት ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ደረሰ ደምሴ እንዳሉት በከተማዋ በተለይም በወተት፣ በዶሮ፣ በዓሣና በንብ መንደሮችን በመለየት የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር እየተከናወነ ይገኛል።

የወተት ምርቱ ከከተማው አልፎ ለይርጋዓለም የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ እንዲሁም ለአዲስ አበባ ገበያ እየዋለ መሆኑን ጠቅሰው እንቁላልም ለተለያዩ አካባቢ ገበያዎች እየቀረበ ነው ብለዋል፡፡


 

የሲዳማ ክልል እንስሳት ሀብት ልማት ቢሮ ምክትልና የእንስሳት ዝርያ ማሻሻልና መኖ ልማት ዘርፍ ኃላፊ አደገ አለሙ(ዶ/ር) በበኩላቸው የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር በክልሉ በሰባት ፓኬጆች ላይ በማተኮር እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

‎ይህንን ውጤታማ ለማድረግ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻል፣ ጤና አጠባበቅና የመኖ ልማት ሥራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑንና የወተት፣ የእንቁላል፣ የማርና ሌሎች ምርቶች መጠን በእጅጉ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።

‎አምና 10 ሚሊዮን ዶሮዎችን በማሰራጨት 500 ሚሊዮን እንቁላል መመረቱን የጠቀሱት ምክትል ቢሮ ሃላፊው ‎በተያዘው በጀት ዓመት ደግሞ 16 ሚሊዮን ዶሮዎችን ለማሰራጨት ታቅዶ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም