ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድን የሚመጥን የአቪዬሽን ደኅንነት አገልግሎት ሰጪ ተቋም እየተገነባ ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 6/2018(ኢዜአ)፦ እያደገ የመጣውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚመጥን የአቪዬሽን ደኅንነት አገልግሎት ሰጪ ተቋም እየተገነባ መሆኑን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ገለጹ።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የሲቪል አቪዬሽን ደኅንነት ዋና መምሪያ አዲስ ያስገነባውን ባለ አምስት ወለል የቢሮ ህንጻ ዛሬ አስመርቋል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀኔራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን የህንጻ ምረቃ ሥነ-ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ በአቪዬሽን ደኅንነት ዘርፍ በተከታታይ ዓመታት በተከናወኑት የሪፎርም ተግባራት በአፍሪካ ምርጥ የአቪዬሽን ደኅንነት አገልግሎት ሰጪ ተቋም እየተገነባ ይገኛል፡፡

በቴክኖሎጂ፤ በመሠረተ ልማት፤ በሰው ኃይል፤ የአሠራር ሥርዓቶችን በማሻሻልና በማዘመን በኩል የተከናወኑት የሪፎርም ሥራዎችና የተገኙት የላቁ ውጤቶችም ይህን ያመላክታሉ።

የሲቪል አቪዬሽን ደኅንነት ዋና መምሪያ የሪፎርም ሥራዎች ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ ለማስቻልም ለአቪዬሽን ዘርፉ አገልግሎት ምቹ የሆነ ሁለገብ ህንጻ መገንባቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አገልግሎት እየሰፋ ከመሄዱ አንጸር ከወዲሁ የሚመጣውን ዕድገት የሚመጥን ዝግጁነት የመኖሩ ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በአቪዬሽን ዘርፍም ሆነ በሌሎች ብሔራዊ ደኅንነትንና ጥቅምን በሚመለከቱ ስምሪቶች በጸጥታና በመረጃ ተቋማት የተገነባው የትብብር መንፈስ ትላልቅ ስጋቶችን በጋራ ለመመከት ማስቻሉን የጠቀሱት አምባሳደር ሬድዋን፤ በቀጣይም እንደ ሀገር የሚገጥሙንን ችግሮች ለመሻገር አጋርነቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ሲሳይ ቶላ በበኩላቸው፤ በሲቪል አቪዬሽን ደኅንነት ዘርፍ የተከናወነው ሪፎርም ኢትዮጵያን እንደ ታላቅነቷ የሚመጥን የአቪዬሽን ደኅንነት አገልግሎት ሰጪ ተቋም እንዲገነባ መሰረት መጣሉን ተናግረዋል፡፡

የአቪዬሽን ደኅንነት ስምሪት ከዘመኑ ጋር ፈጥኖ መገኘትን ይፈልጋል ያሉት አቶ ሲሳይ፤ ለምረቃ የበቃው ባለ አምስት ወለል የቢሮ ሕንጻ ዘመኑ የሚጠይቀው ቴክኖሎጂ የተሟሉለትና ለወደፊቱም ተለዋወጭ የቴክኖሎጂ ሁኔታዎችን ታሳቢ በማድረግ ለቁጥጥርና ክትትል አመቺ ሆኖ የተገነባ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የሲቪል አቪዬሽን ደኅንነት ዋና መምሪያ ዳይሬክተር አቶ አስራት ቀጀላ በበኩላቸው፤ ህንፃው ደረጃውን ጠብቆ መገንባቱ ምቹ የስራ ከባቢ ከመፍጠሩ ባሻገር በዘረፉ እንደ ሀገር ያለውን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይና ተቋማዊ ገጽታን በማጉላት ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው አመልክተዋል፡፡

ከአፍሪካ ምርጥ የአቪዬሽን ደኅንነት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መካከል አንዱ ለመሆን የተያዘውን ስትራቴጂክ ግብ እውን ለማድረግ እንደሚያግዝም ተናግረዋል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ደኅንነቱ የተጠበቀና ዓለም አቀፍ መስፈርትን መሰረት ያደረገ የደኅንነት አገልግሎት በመስጠት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዘርፉ የአፍሪካ ኩራት ሆኖ የመሪነት ደረጃውን እንዲይዝ፣ በተወዳጅነትና በተመራጭነት እንዲቀጥል የጀርባ አጥንት ሆኖ የበኩሉን ተቋማዊ ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝም አመልክተዋል፡፡

በሲቪል አቪዬሽን ደኅንነት ዋና መምሪያ ህንጻ ግንባታ ተሳትፎ ያደረጉት ሁሉም አካላት በተለይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በብዙ መልኩ ላደረገው እገዛ በምረቃ መርሀ-ግብሩ ላይ ከፍተኛ ምስጋና እንደተቸራቸው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለኢዜአ በላከው መረጃ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም