ቀጥታ፡

በክልሉ እየተተገበረ የሚገኘውን የማከምና የመከላከል ፖሊሲ ውጤታማ ለማድረግ የጤና ተቋማትን ደረጃ የማሻሻል ስራ እየተሰራ ነው

ደሴ፤ ህዳር 6/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል እየተተገበረ የሚገኘውን የማከምና የመከላከል ፖሊሲ ውጤታማ ለማድረግ የጤና ተቋማትን ደረጃ የማሻሻል ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ከ200 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የተገነቡ የጤና ተቋማትን ዛሬ አስመርቋል።


 

በዚሁ መርሃ ግብር ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አብዱልከሪም መንግስቱ በክልሉ እየተተገበረ የሚገኘውን የማከምና የመከላከል ፖሊሲ ውጤታማ ለማድረግ የጤና ተቋማትን ደረጃ የማሻሻል ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።


 

በዚህም በክልሉ በ221 ጤና ተቋማት ላይ የማስፋፊያ እና ደረጃን የማሻሻል ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው የ97ቱ ግንባታ መጠናቀቁን ተናግረዋል።

ለዚህም በደሴ ዛሬ የተመረቁት የጤና ተቋማት ግንባታ እና ማስፋፊያ ስራዎች አብነት መሆናቸውን አንስተዋል።


 

በደሴ ከተማ የጤና ተቋማትን ደረጃ በማሻሻልና በማስፋፋት ለህብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉን የገለጹት ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ ናቸው።

የጤና ተቋማትን ተደራሽ በማድረግና ደረጃቸውን በማሻሻል ለህብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ ይገኛልም ነው ያሉት።

በዚህም ከ200 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የተገነቡ ዘመናዊ የጤና ጣቢያ፣ የጤና ጣቢያ ማስፋፊያዎች፣ የደረጃ ማሻሻያዎችና ጤና ኬላዎች ዛሬ መመረቃቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

ዛሬ ከተመረቁት የጤና ተቋማት መካከል አንድ አዲስ ጤና ጣቢያ፣ አምስት አዲስ ጤና ኬላ፣ ሰባት የጤና ጣቢያ ማስፋፊያዎችና የደረጃ ማሻሻል ስራዎች እንዲሁም ሁለት የቀዶ ህክምና አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ይገኙበታል ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም