ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት እንድትሆን እንደ ሀገር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል - ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ(ዶ/ር)

ባሕር ዳር፤ ህዳር 6/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት እንድትሆን እንደ ሀገር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ(ዶ/ር) ገለጹ።

የባሕር በር ባለቤትነት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የማስጠበቅ የሕልውና ጉዳይ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

ጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ምላሽ እና ማብራሪያ የቀይ ባሕር ጉዳይ ሕጋዊ፣ ታሪከዊ፣ መልክዓ ምድራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል።

ኢትዮጵያ ካላት የሕዝብ ቁጥር አንፃር የባሕር በርን በሰላማዊ እና ሕጋዊ መንገድ ማግኘት የሚያስችላት አካሄድም ሆነ አሰራር እንዳለ ተመልክቷል።

አሁን በኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን ኢኮኖሚ የሚመጥን የወጪና ገቢ ዕቃዎችን ማስተናገድ የሚችል የባሕር በር አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት እንደ ሀገር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ እንደሚገኝ ሚኒስትሩ ዓለሙ ስሜ(ዶ/ር) ገልጸዋል። 

ሚኒስትሩ በባሕር ዳር በተካሄደ የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ዘርፍ ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ መድረክ እንዳመለከቱት፤ አሁን ላይ ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባውም ሆነ ወደ ውጭ የምትልከው ምርት በዓይነትም ሆነ በመጠን በእጅጉ ጨምሯል።

ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፍ በእጅጉ እያደገች መሆኑን ጠቁመው ይህን ማስተናገድ የሚችል ብዙ ወደብ ያስፈልጋታል ሲሉም ተናግረዋል።

መንግስት ኢትዮጵያ የባሕር በር እንደሚያስፈልጋት አምኖ በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን በመግለጽ ይህን ጥረት ሁሉም ዜጋ ሊደግፈው ይገባል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም