ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል ጥራት ያለው የላብራቶሪ አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል ተግባር እየተከናወነ ነው_ የጤና ቢሮ

አዳማ ፤ ሕዳር 6/2018 (ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል በየደረጃው በሚገኙ የህክምና ተቋማት ጥራት ያለው የላብራቶሪ አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል ተግባር እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ በጤና ተቋማት እየተሰጠ ያለውን የላብራቶሪ አገልግሎት የሚገመግም መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።

የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ተስፋዬ ክበበው እንዳሉት፤ ለሕክምና ውሳኔ አሰጣጥ ጥራት ያለው የላብራቶሪ አገልግሎት ወሳኝ ነው።

በተለይ የላብራቶሪ አገልግሎት የታካሚን የጤና ሁኔታ የምናይበት እና የመድኃኒትን ውጤታማነት የምንከታተልበት የሕክምናው ዋና መሰረት በመሆኑ በየደረጃው ሕክምና ተቋማት የሚሰጠው አገልግሎት ጥራቱ የተጠበቀ እንዲሆን እየተሰራ እንደሚገኝ  ነው ያስታወቁት።

በተለይም የድንገተኛ የጤና ወረርሽኞች በሚከሰቱበት ወቅት ፈጣን  ልየታ በማድረግ ምላሽ የምንሰጥበት በመሆኑ ጥራት ያለው የላብራቶሪ ምርመራ ለሕክምና አገልግሎት ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል።

ለዚሕም በክልሉ የሚገኙ ጤና ተቋማት ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት ለማኅበረሰብ እንዲሰጡ ዘመናዊ የላብራቶሪ ግብዓቶችን ተደራሽ ማድረግ ቀዳሚ ተግባር ተደርጎ መሠራቱን አስታውቀዋል።

በተለይ ቢሮው ከባለድርሻ አከላት ጋር በመቀናጀት በክልሉ የሕክምና ሥርዓቱን ለማዘመን የላብራቶሪ አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ እና ለባለሙያ ሥልጠናዎች እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

በጤና ተቋማት በየጊዜው የሚደረጉ ድጋፍና ክትትል ስራዎች በትኩረት በመሰራታቸው የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉንም ገልጸዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የቢሾፍቱ አጠቃላይ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ታደሰ ጎንፋ፤ በዘመናዊ ሕክምና ከ60 እስከ 70 በመቶ የሚሆነው የሕመም ልይታው የሚካሄደው በላብራቶሪ ላይ የተመሰረተ ነው ብለዋል።

ጥራት ያለው ሕክምና ለመስጠት የላብራቶሪ መዘመን አጅግ አስፈላጊ በመሆኑ ሆስፒታሉ  ዘመናዊ ማሽኖችንና ብቃት ያለው የሰው ሃይል በመመደብ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

ሌላኛው ተሳታፊ የጊነር አጠቃላይ ሆስፒታል ሥራ እስኪያጅ አቶ ኑር ዛላም፤ የታማሚን ደሕንነት ለማስጠበቅ ሆስፒታሉ ጥራት ያለው የላብራቶሪ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።

በተለይ ሆስፒታሉ ጥራት ያለው የላብራቶሪ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ በተሰራው የ"አክሪዴሽን " ምዘና ውጤታማ መሆኑን ጠቅሰው፤  በቀጣይም ባለሙያዎችን በአግባቡ በመያዝ የጥራት ደረጃውን ለማሻሻል እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም