ሰራዊታችን በባንዳነት በተሰለፈው ፅንፈኛ ቡድን ላይ እርምጃ በመውሰድ ሰላምን እያፀና ነው - ሌተናል ጄኔራል መሀመድ ተሰማ - ኢዜአ አማርኛ
ሰራዊታችን በባንዳነት በተሰለፈው ፅንፈኛ ቡድን ላይ እርምጃ በመውሰድ ሰላምን እያፀና ነው - ሌተናል ጄኔራል መሀመድ ተሰማ
ባሕርዳር፤ ህዳር 6/2018(ኢዜአ)፡- ሰራዊቱ የኢትዮዽያ ታሪካዊ ጠላቶች ተላላኪ በመሆን በባንዳነት በተሰለፈው ፅንፈኛ ቡድን ላይ ተከታትሎ እርምጃ በመውሰድ ሰላምን በዘላቂነት እያፀና መሆኑን የምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል መሀመድ ተሰማ ገለጹ፡፡
ሌተናል ጄኔራል መሀመድ ተሰማ፤ በሰሜን ጎጃም እና በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞኖች በግዳጅ ላይ የሚገኘውን ኮር የግዳጅ አፈጻጸም የመስክ ምልከታ አድርገዋል።
ከመስክ ምልከታቸውም በኋላ ከዞንና ከወረዳ አመራሮች እንዲሁም ሌሎች አመራሮች ጋር የተወያዩ ሲሆን በሰሜን አቸፈር ወረዳ ሊበን ከተማ በአንድ ክፍለ ጦር የስልጠና ማጠናቀቂያ ላይ በመገኘትም የስራ መመሪያና ስምሪት ሰጥተዋል።
ሌተናል ጄኔራሉ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ ሰራዊቱ የኢትዮዽያ ታሪካዊ ጠላቶች ተላላኪ በመሆን በባንዳነት የተሰለፈውን ፅንፈኛ ቡድን ተከታትሎ እርምጃ በመውሰድ ሰላምን በዘላቂነት እያፀና ይገኛል ብለዋል።
በተለያዩ አካባቢዎች በመሽሎክሎክ ሕብረተሰቡን በማገትና በመዝረፍ ወንጀል የሚፈፅመውን ፅንፈኛ ቡድን ሰራዊቱ ከሕዝቡ ጋር በመተባበር ተከታትሎ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን አንስተው፤ ይህም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።
የታሪካዊ ጠላቶችን ተልዕኮ በመቀበል በክህደት በዜጎች ላይ ወንጀል ለመፈፀም የሚንቀሳቀሰውን ፅንፈኛ ቡድን በየደረጃው የሚገኘው አመራር፣ ሕዝቡና የፀጥታ ሃይሉ በትብብር ሕግ የማስከበር ስራውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።
በኢትዮዽያ ሁሉም አካባቢዎች ሰላምን በማፅናትና የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶችን በማሳካት የኢትዮጵያን እድገትና ብልፅግና ማረጋገጥ የሁላችንም አደራ እና ሃላፊነት ሊሆን ይገባል ብለዋል።
የሰላምና የጀግንነት ተምሳሌት የሆነው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ለኢትዮዽያ ክብርና ሉአላዊነት መከበር ከመቼውም ጊዜ በላይ በላቀ ዝግጁነት የሚገኝ መሆኑን ሌተናል ጄኔራል መሀመድ ተሰማ አረጋግጠዋል።