ቀጥታ፡

የድሬዳዋ ልማትና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የወጣቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል - ከንቲባ ከድር ጁሃር 

ድሬደዋ፤ ህዳር 6/2018(ኢዜአ)፦ የድሬዳዋ ልማትና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የወጣቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ትኩረት መሰጠቱን  የድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ተናገሩ።

የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶች ምክር ቤት ሁለተኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ዛሬ መካሄድ ጀምሯል።

ጉባኤው በሁለት ቀናት ቆይታው በአገርና በድሬዳዋ ልማት፣ ሰላም እና ዘላቂ ዕድገት ላይ ወጣቱ ያለውን አበርክቶ እና ተጠቃሚነት ይገመግማል ተብሏል።

በጉባኤ ላይ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር እንደተናገሩት ወጣቶች የድሬደዋን የብልጽግና ጉዞና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የላቀ ሚናቸውን እየተወጡ ናቸው።

ወጣቶች በድሬዳዋ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ያላቸውን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማስቀጠልም አስተዳደሩ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

አገራዊ ለውጡ  ወጣቶች  በግልና በማህበር ታቅፈው በገጠርና በከተማ ልማት እንዲሳተፉ ማገዙን የገለጹት፤ ደግሞ የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽነር ካሊድ መሐመድ ናቸው።

ወጣቶች በበጋ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በመሳተፍ  የአረጋውያንን ቤቶች በመገንባት፣ ደም በመለገስ፣ ማዕድ በማጋራት፣ ከፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር ሰላምን በማረጋገጥ ላይ በንቃት በመሳተፍ ማህበራዊ ሀላፊነታቸውን እየተወጡ መሆናቸውን  አንስተዋል።

እነዚህን ስራዎች ከማጠናከር ጎን ለጎን በሁሉም ዘርፍ ያላቸውን ተጠቃሚነት ለማጎልበት ጉባኤው መሠረታዊ አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥ ተናግረዋል ።

የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ወጣት ሃሚድ አብደላ በበኩሉ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ ለወጣቶች የተሰጠው ትኩረት የወጣቱን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት እያሳደገ መሆኑን አንስቷል።

እነዚህን እንቅስቃሴዎች በማጠናከር የድሬዳዋን ዘላቂ ሰላምና የልማት ጉዞ ከዳር ለማድረስ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አስታውቋል።

ለሁለት ቀናት የሚካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ በአገራዊ መሠረታዊ አቅጣጫዎች ላይ በመወያየት የተሻለ ስራ ለማከናወን የሚያስችል ሁኔታ የሚፈጠር መሆኑን በማረጋገጥ ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም