በክልሉ የጋራ ትርክት ግንባታን በማጠናከር ዘላቂ ሰላምና ልማትን እውን ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቷል - ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የጋራ ትርክት ግንባታን በማጠናከር ዘላቂ ሰላምና ልማትን እውን ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቷል - ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ
ጋምቤላ፤ ህዳር 6/2018(ኢዜአ)፦ በጋምቤላ ክልል የጋራ ትርክት ግንባታን በማጠናከር ዘላቂ ሰላምና ልማትን እውን ለማድረግ ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ ገለጹ።
በክልሉ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ውይይት አካሂደዋል።
ርዕሰ መስተዳድሯ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የክልሉ ህዝብ አንድነቱንና አብሮነቱን በማጠናከር መንግስት የጀመረውን የዘላቂ ሰላም ግንባታና የልማት ስራዎች ማገዝ ይጠበቅበታል።
የክልሉ አመራርም የአስተሳሰብና የተግባር አንድነቱን በማጠናከር በክልሉ የታለሙ የልማትና የመልካም አስተዳደር እቅዶችን ዳር ለማድረስ ከምንጊዜውም በላይ በቁርጠኝነት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
በክልሉ የጋራ ትርክት ግንባታን በማጠናከር ዘላቂ ሰላምና ልማትን እውን ለማድረግ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ ነው ያሉት።
በክልሉ የሚፈለገውን ልማትና እድገት ማሳካት የሚቻላው ዘላቂ ሰላምን ማስፈን ሲቻል መሆኑን ጠቁመው የክልሉን ሰላም ለማደናቀፍ የሚሰሩ አካላትን በጋራ መታገል ይገባል ብለዋል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጋትሉዋክ ሮን(ዶ/ር) በበኩላቸው ዘላቂ ሰላም በማስፈን የተጀመሩ የልማት እቅዶችን ለማሳካት ህዝብን አስተባብረን ልንሰራ ይገባል ነው ያሉት።
በተለይም የክልሉን ሰላም ለማወክ የሚሰሩ አካላትን እኩይ ተግባር በመመከቱ ረገድ ሁሉም በጋራ ተባብሮ መስራት እንደለበት ገልጸዋል።
የጋራ ትርክት ግንባታ ስራዎችን በማጎልበት መልካም እሴቶችን ማጠናከር ላይ ትኩረት አድረጎ መሰራት እንዳለበት ያመለከቱት ደግሞ የክልሉ መንግስት የዴሞክራሲ ግንባታ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አሸኔ አስቲን ናቸው።