በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የመሠረተ ልማት ስራዎች እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የመሠረተ ልማት ስራዎች እየተከናወኑ ነው
አሶሳ፤ ህዳር 6/2018(ኢዜአ)፦ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የመሠረተ ልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ተናገሩ።
ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ ኡራ ወረዳ ቁሽመንገል ቀበሌ አነስተኛ የመስኖ ፕሮጀክት የግንባታ አስጀምረዋል።
በተጨማሪም በወረዳው አሉቦ ቀበሌ የተገነባውን የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀከት መርቀው ከፍተዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን በወቅቱ እንደተናገሩት፤ በክልሉ የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የተለያዩ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
የኡራ ወረዳ ከመደበኛ የግብርና ስራ በተጨማሪ ለመስኖ የሚያገለግል የውሃ ሀብት ያለው በመሆኑ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ማልማት እንደሚቻል ተናግረዋል።
አነስተኛ የመስኖ ግንባታ ፕሮጀክቱ በአካባቢው መልማት የሚችለውን ሰፊ ማሳ በማልማት የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ባበክር ሀሊፋ በበኩላቸው፤ አነስተኛ የመስኖ ግንባታ ፕሮጀክቶች የአርሶ አደሩን የማምረት አቅም የሚያሳድግ መሆኑን ጠቁመዋል።
በ169 ሚሊዮን ብር የሚገነባው ፕሮጀክቱ 200 ሄክታር መሬት ማልማት የሚችል ሲሆን የቁሽመንገል እና የአሉቦ ቀበሌ አርሶ ደሮችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በተጨማሪም በወረዳው አሉቦ ቀበሌ የተገነባውን የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ስራ ያስጀመሩ ሲሆን ፕሮጀክቱ የህብረተሰቡን ማህበራዊ ችግር የሚያቃልል እንደሆነም ገልጸዋል።
የቀበሌው ነዋሪ አለዊያ ሱሌማን እና አሃያ ሉቅማን እንደተናገሩት ከዚህ ቀደም የመጠጥ ውሃ ለማግኘት ብዙ ርቀት በመጓዝ ለእንግልት ሲዳረጉ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
አሁን በአቅራቢያቸው የተገነባላቸው የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ከዚህ በፊት የነበረባቸውን ችግር በመፍታት ንፁህ ውሃ ለማግኘት እንዳስቻላቸው ገልጸዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ በብልጽግና ፓርቲ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢሳቅ አብዱልቃድር፣ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እና የአካባቢው የማህበረሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።