የመዲናዋን የጤና ቱሪዝም መዳረሻነትን ዕውን የሚያደርጉ ስኬታማ ስራዎች እየተከናወኑ ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
የመዲናዋን የጤና ቱሪዝም መዳረሻነትን ዕውን የሚያደርጉ ስኬታማ ስራዎች እየተከናወኑ ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 6/2018(ኢዜአ)፦ የመዲናዋን የጤና ቱሪዝም መዳረሻነትን ዕውን የሚያደርጉ ስኬታማ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የዘውዲቱ መታሠቢያ ሆስፒታል የላቀ የሕክምና ማዕከል የማስፋፊያ ግንባታ መርቀዋል።
ዛሬ የተመረቀው የማስፋፊያ ግንባታ የሆስፒታሉን የአገልግሎት አሰጣጥን ከእጥፍ በላይ የሚያልቅ መሆኑም ተጠቁሟል።
ከንቲባ አዳነች በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የዘውዲቱ መታሠቢያ ሆስፒታልን በአዲስ ግንባታ እና በዘመናዊ የሕክምና መሣሪያዎች ማሟላት ተችሏል።
ሆስፒታሉ ለተገልጋዮችና ለባለሙያዎች እጅግ ምቹ በሆነ መንገድ መገንባቱን ጠቁመዋል።
አዲስ አበባን የብልጽግና ማዕከል ለማድረግ በሁሉም ዘርፎች የተጀመሩ ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን አንስተው፤ በጤናው ዘርፍም አርዓያ የሚሆኑ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አንስተዋል።
የጤና ተቋማትን ከማስፋፋት እና ደረጃቸውን የጠበቁ ከማድረግ ጎን ለጎን የህዝብን ጤና ማስጠበቅ የሚያስችሉ ጽዱ ከተማ እየተገነባ ይገኛል ብለዋል።
ባለፉት ዓመታት የጤና ተቋማትን ደረጃ ለማሻሻል እና ጥራትን ለማስጠበቅ የተሰሩ ስራዎች አብነት መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በዚህም በከተማዋ 28 የጤና ተቋማት ተጠናቀው ወደ ስራ መግባት መቻላቸውን ጠቁመው፤ የዘውዲቱ መታሠቢያ ሆስፒታል ግንባታም ሆስፒታሉን የልህቀት ማዕከል ማድረግ የሚያስችል ነው ብለዋል።
አዲስ አበባን የጤና ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው እንዳሉት፤ የሆስፒታሉ ማስፋፊያ ግንባታ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ብሎም በርካታ ችግሮችን የሚፈታ ነው።
በሽታ ከመከላከል ጎን ለጎን አክሞ የማዳንን ፖሊስ ተግባራዊ መደረጉን ሚኒስትሯ ጠቁመው፤ ለዚህ ስኬትም የጤና ማዕከላትን ማስፋፋት ዓይነተኛ ግብ ነው ብለዋል።
ባለፉት ዓመታት ለጤናው ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት መሰጠቱን ጠቁመው፤ ሦስት ብቻ የነበረውን የኦክስጂን ፕላንት ወደ 57 ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል።
በጤናው ዘርፍ ኢትዮጵያን የሚመጥን ታሪክ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸው፤ ከተደራሽነት፣ ጥራት እና ፍትሃዊነት አኳያ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሐንስ ጫላ በበኩላቸው፤ በመዲናዋ በጤናው ዘርፍ ተደራሽነትን፣ ፍትሐዊነትን እና ጥራትን መሠረት ያደረጉ ውጤታማ ሥራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል።
የዘውዲቱ መታሠቢያ ሆስፒታል ማስፋፊያ ግንባታ ከተማዋን የሚመጥን የጤና አገልግሎት ለማቅረብ እና የጤና ቱሪዝም ራዕይን ለማሳካት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቁመዋል።
የዘውዲቱ መታሠቢያ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ቴዎድሮስ አቡሌ በበኩላቸው፤ ፕሮጀክቱ የሆስፒታሉን የአገልግሎት አሰጣጥ በሁሉም መስክ በሁለት እጥፍ እንደሚያሳድግ ገልጸዋል።
በማስፋፊያው 320 ተጨማሪ ሕክምና መስጫ አልጋዎች መካተታቸውንም አመላክተዋል።
የዘውዲቱ መታሠቢያ ሆስፒታል የላቀ የሕክምና ማዕከል የማስፋፊያ ግንባታ ባለ አስር ወለል ህንጻ ሲሆን፤ ዘመናዊ የህክምና መሣሪያዎች የተሟሉለት ነው።