ቀጥታ፡

የጁገል መልሶ ልማት በሕዝብ ተሳትፎ ውጤታማ የሆነ አርአያነት ያለው ተግባር ነው - ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ

ሐረሪ፤ ህዳር 6/2018(ኢዜአ)፡ - የጁገል መልሶ ልማትና እንክብካቤ ስራ በሕዝብ ተሳትፎ ውጤታማ የሆነ አርአያነት ያለው ተግባር መሆኑን የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለጹ።

በሐረሪ ክልል 4ኛ ዙር የጁገል አለም አቀፍ ቅርስ ኮሪደር እና የሐረር ከተማ ወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክቶችን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ አስጀምረዋል።


 

ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ፤ የመደመር መንግሥት እይታ ፀጋዎችን እንድንጠቀም አዳዲስ እሳቤዎችን ይዞ የመጣ ነው ብለዋል።

ከዚህ በፊት በክልሉ በተከናወኑ የኮሪደር ልማት ሥራዎች በርካታ ውጤቶች መገኘታቸውን ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በተለይም በሐረር ከተማ የተከናወነው ስራ የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎችን ቁጥር ማሳደጉን ተናግረዋል።

የኮሪደር ልማት ስራው የሐረር ከተማን ለነዋሪውና ለጎብኚዎች ምቹ ከማድረግ ባሻገር ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠረ መሆኑንም አንስተዋል።

የጁገል መልሶ ልማትና እንክብካቤ እንዲሁም የኮሪደር ልማት ሥራው ላይ የሕብረተሰቡ ቅንጅታዊ ተሳትፎ ውጤታማ የሆነ አርአያነት ያለው ተግባር መሆኑን ገልጸው ይህም በቀጣይ በምንሰራቸው ስራዎች ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

በቀጣይ የምንሰራቸው ሐረርን መልሶ የማልማት ሥራና በከተማዋ በሚገኙ ወንዞች ላይ የሚከናወነው የወንዝ ዳር ፕሮጀክት እውን እንዲሆን ሁሉም ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።


 

የልማት ሥራዎቹ መፍጠንና መፍጠርን ታሳቢ በማድረግ መሰራት እንዳለባቸው ያሳሰቡት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በከተማዋ የሚከናወነው አራተኛው ሐረርን መልሶ የማልማት የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክት ከዚህ ቀደም የነበሩት ምርጥ ተሞክሮዎችን በመውሰድና ክፍተቶችን በማረም ይከናወናል ብለዋል።

የክልሉ አመራሮችም እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ አሁን ላይ የተጀመሩ ሥራዎች በወቅቱ እንዲጠናቀቁ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በተያያዘም በክልሉ በበጀት ዓመቱ ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች መካከል የወንዝ ዳርቻ ልማት አንዱ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ይህም የሕዝብን ተጠቃሚነት ማዕከል ባደረገ መልኩ በጥራትና በፍጥነት እንደሚከናወን ገልጸዋል።


 

ፈጠራና ፍጥነት የብልጽግና ፓርቲ መርህ መሆኑን የገለፁት ደግሞ በፓርቲው የሐረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ጌቱ ወዬሳ ናቸው።

ፓርቲው ሁለንተናዊ ብልፅግናን በማረጋገጥ የሕዝብን ሁሉ አቀፍ ተጠቃሚነት ለማስፋት አበክሮ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

የክልሉ ባሕል፣ ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ ተወለዳ አብዶሽ፤ በ3 ዙሮች በተከናወነው የጁገል ኮሪደር ልማት ከ13ሺህ ሜትር በላይ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን መልሶ ማልማት ተችሏል ነው ያሉት።

የ4ኛው ዙር የተቀናጀ የጁገል ኮሪደርን ካለፉት 3 ዙሮች ትምህርት በመውሰድ በተሻለ ጥራትና ፍጥነት ለመስራት ርብርብ ይደረጋል ብለዋል።

የሐረር ከተማ ማዘጋጃ ቤት ስራ አስኪያጅ ያህያ አብዱረሂም፤ የወንዝ ዳርቻ ልማቱ ምንጮችን በማጎልበት፣ አረንጓዴ ስፍራዎችን በማልማትና ምቹ የመኖሪያ አካባቢዎችን በማስፋት ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ናቸው ብለዋል።

4ኛው ዙር የጁገል ኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት ስራዎችን በ60 ቀናት ለማጠናቀቅ ርብርብ እንደሚደረግም ተመላክቷል።

በፕሮጀክቶቹ ማስጀመሪያ መርሐ-ግብር ላይ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ሱልጣን አብዱሰላም፣ የሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ አፈ ጉባዔ ሙህየዲን አህመድ፣ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሰላህዲን ተውፊቅ፣ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሮዛ ኡመርን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም