ከተሞች በመሰረተ ልማት የተሟሉ እንዲሆኑ ጠንካራ መሰረት ያለው ስራ እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ከተሞች በመሰረተ ልማት የተሟሉ እንዲሆኑ ጠንካራ መሰረት ያለው ስራ እየተከናወነ ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 6/2018(ኢዜአ)፦ ከተሞች በመሰረተ ልማት የተሟሉ እንዲሆኑ ጠንካራ መሰረት ያለው ስራ እየተከናወነ መሆኑን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ገለጹ።
10ኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም "የከተሞች ዕድገት ለኢትዮጵያ ልህቀት” በሚል መሪ ሀሳብ በአፋር ክልል ሰመራ ሎጊያ ከተማ መካሄድ ጀምሯል፡፡
በመርሀ ግብሩ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ፣ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ዘሀራ ኡመድ እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች ታድመዋል።
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የብልጽግና መደላድል እየፈጠሩ ካሉ ሀገራት አንዷ ናት።
በመሰረተ ልማት ደረጃም ዘመናዊ ማዕከላት እየተገነቡ መሆናቸውን አንስተው፤ ከተሞችን የብልጽግና ማዕከል ለማድረግ ሰፋፊ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።
የከተሞች ፎረም የእርስ በእርስ ትውውቅ እንዲጠናከር ከተሞች ተሞክሮ እንዲለዋወጡ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተናግረዋል።
ከተሞች በመሰረተ ልማት የተሟሉ እንዲሆኑ ጠንካራ መሰረት ያለው ስራ እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።
ከተሞች የብልጽግና ማዕከል እንዲሆኑ ሁሉን አቀፍ ጥረቶች እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም ወቅቱ የሚጠይቀው አስተሳሰብ መሆኑን ጠቁመዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጭነት የተጀመረው የኮሪደር ልማት የማንሰራራት ተምሳሌት የሆነ ስራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የኮሪደር ልማት በውስጡ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮችን የያዘ የልማት እሳቤ መሆኑን ተናግረዋል።
ተወዳዳሪ የሆኑ ከተሞችን ለማፍራት እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ፎረሙ የተጀመሩ ስራዎችን ይበልጥ ለማጎልበት ቃል የምንገባበት መሆን አለበትም ብለዋል።
የሰመራ ሎጊያ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አብዱ ሙሳ በበኩላቸው፤ መንግስት ለመሰረተ ልማት በሰጠው ልዩ ትኩረት ከፍተኛ ለውጥ እየተመዘገበ ነው ብለዋል።
የሰመራ ከተማ በምሳሌነት እንድትጠቀስው የከተማዋ ኮሪደር ልማት ላይ በከፍተኛ ርብርብ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም የከተማዋን የወጭ ገቢ ማዕከልነት የሚመጥኑ የመሰረተ ልማት ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።