በአማራ ክልል የተገነቡት የሕዝብ መድሐኒት ቤቶች ሕብረተሰቡን በተመጣጣኝ ዋጋና በቅርበት እያገለገሉ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የተገነቡት የሕዝብ መድሐኒት ቤቶች ሕብረተሰቡን በተመጣጣኝ ዋጋና በቅርበት እያገለገሉ ናቸው
ደሴ፤ ህዳር 6/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የተገነቡት የሕዝብ መድሐኒት ቤቶች ሕብረተሰቡን በተመጣጣኝ ዋጋና በቅርበት እያገለገሉ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣታቸውን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።
በደሴ ከተማ ከ100 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የተገነቡ የሕዝብ መድሐኒት ቤቶች ዛሬ ተመርቀዋል።
በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ እንደገለጹት፤ በክልሉ 238 የሕዝብ መድሐኒት ቤቶችን በመገንባት ወደ ሥራ የማስገባቱ ተግባር ቀጥሏል።
ከእነዚህም መካከልም እስካሁን 58 የሕዝብ መድሐኒት ቤቶች ወደ ሥራ እንደገዲገቡ መደረጉን ተናግረዋል።
የሕዝብ መድሐኒት ቤቶቹ መገንባት ለሕብረተሰቡ በቅርበት አገልግሎት በመስጠት መድሐኒቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረቡ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣታቸውን አስታውቀዋል።
መድሐኒት ቤቶቹን ከመድሐኒት አቅራቢ ድርጅቶች ጋር በማስተሳሰር ጭምር የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ መሆኑንም አንስተዋል።
ዛሬ በደሴ ከተማ የተመረቁት የሕዝብ መድሐኒት ቤቶችም ደረጃቸውን የጠበቁና ለሌሎች አካባቢዎች ሞዴል የሚሆኑ ናቸው ብለዋል።
የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ በበኩላቸው፤ ዛሬ የተመረቁት የሕዝብ መድሐኒት ቤቶች ከ100 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የተገነቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ከተመረቁት መካከል አንዱ ዛሬ በይፋ ስራ መጀመሩን ጠቅሰው፤ ቀሪዎቹ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ አገልግሎት እንደሚጀምሩ አስታውቀዋል።
መድሐኒት ቤቶችን በተሻለ በማደራጀት ለከተማዋ ነዋሪ ከሚሰጡት አገልግሎት በተጨማሪ ለአጎራባች አካባቢዎች መድሐኒት ማከፋፈል እንዲችሉ ጭምር ግብ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
በምረቃ መርሃ ግብሩ የክልልና የከተማ አስተዳደሩ አመራሮችን ጨምሮ ባለድርሻ አካላትም ተገኝተዋል።