መንግስት የተለማቸው ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ምርታማነትን በማሳደግ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር ትልቅ አቅም ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት የተለማቸው ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ምርታማነትን በማሳደግ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር ትልቅ አቅም ናቸው
ጭሮ፤ ህዳር 6/2018(ኢዜአ)፦ መንግስት የተለማቸው ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ምርታማነት በማሳደግ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር ትልቅ አቅም እንደሚሆኑ ምሁራን ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያነጋገራቸው ምሁራን እንዳሉት መንግስት የተለማቸው ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር በውስጥ ለማምረት የሚያስፈልግ ግብዓትን በማምረት ፍላጎት መር የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር እንደሚያስችሉ ተናግረዋል፡፡
በኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር ጅፋራ ለሜሳ እንዳሉት ሀገሪቱ ልማቷን ለማፋጠን ከውጪ የምታስገባቸውን ማዳበርያ እና ነዳጅ ምርቶችን በሀገር ምርት ለመተካት ያቀደቻቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች ሲወጣ ነበረውን የውጪ ምንዛሪ ማስቀረት ያስችላል።
የፍላጎት መር የገበያ ዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር ምርታማነትን ማሳደግና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት የሚያስፈልግን ጥሬ እቃ ለማምረት ትልቅ አቅም እንደሚሆኑ አክለዋል።
ለዚህም የማዳበርያ ፋብሪካና የተፈጥሮ ጋዝ ማጣርያ ፕሮጀክቶች ትልቅ አስተዋጽኦ ያላቸው መሆኑን በማሳያነት አቅርበዋል፡፡
መንግስት የወጠናቸው የልማት ፕሮጀክቶች የሀገሪቱን ብልጽግና ለማረጋገጥ መሰረት መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የሶሻል ሳይንስ ኮሌጅ አስተባባሪ ፈቃዱ ወርቁ ናቸው፡፡
ዘመናዊ ዓለም ዓቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ እና የኒኩሊየር ፕላንት እንዲሁም የቱሪዝም እምቅ ሀብቶች ልማት ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት ድርሻቸው ትልቅ ነው ብለዋል።
በኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ መምህር እና ተመራማሪ ንጉሴ ደበሌ(ዶ/ር) መንግስት የመኖሪያ ቤቶች ግንባታና ዘመናዊ የአውሮፕላን ማረፊያ ለመገንባት የጀመረው እንቅስቃሴ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማቱን በማፋጠን ትልቅ ተስፋ የሚጣልበት ነው ብለዋል፡፡
ባለፉት ሰባት የለውጥ አመታት ትላልቅ ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶችን ከማከናወን ባለፈ በተያዘላቸው የግዜ ገደብ መጠናቀቃቸው የሀገሪቱን ትላልቅ ፕሮጀክቶችን የመፈጸም አቅም ያሳየ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
የማዳበርያ ፋብሪካ እና በተፈጥሮ ጋዝ ማጣርያ ፕሮጀክቶች ግንባታም እየተመዘገበ ያለውን ከፍተኛ የበጋ ስንዴ ልማትን በማጠናከር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡
ይህም የሀገሪቱን አስተማማኝ የኢኮኖሚ ዕድገት በመገንባት ለመጪው ትውልድ ያደገች ሀገር ማስረከብ እንደሚያስችል አመልክተዋል፡፡