የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ምክንያታዊና ዓለም አቀፍ የውሃ ሃብት አጠቃቀም ህግን መሠረት ያደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ምክንያታዊና ዓለም አቀፍ የውሃ ሃብት አጠቃቀም ህግን መሠረት ያደረገ ነው
አክሱም፤ ህዳር 6/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ምክንያታዊና ዓለም አቀፍ የውሃ ሃብት አጠቃቀም ህግን መሠረት ያደረገ መሆኑን በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህርና ተመራማሪ ካህሳይ ገብረህይወት ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ ኢትዮጵያ የባሕር በር ተዘግቶባት መኖር የማትችል መሆኑንና የባህር በር ባለቤት መሆኗ እንደማይቀር መግለፃቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ደግሞ በቀጣናው አብሮ ለማደግና ለጋራ ተጠቃሚነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አስረድተዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ለምላሹ የመንግስት ጥረት ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ማረጋገጣቸው ይታወሳል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህርና ተመራማሪ ካህሳይ ገብረህይወት፤ በባህር በር ጉዳይ የመንግስትን አቋምና ቁርጠኝነት በማድነቅ ምላሽ ማግኘት ያለበት ጥያቄ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ በየትኛውም መመዘኛ ተገቢ መሆኑን አንስተው ምክንያታዊና ዓለም አቀፍ የውሃ ሃብት አጠቃቀም ህግን መሠረት ያደረገ መሆኑንም አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ለ30 ዓመታት ተዳፍኖ መቆየቱ እና ተዘግቶባት መቆየቷ ብዙ ዋጋ ያስከፈላት መሆኑን አንስተው አሁን ላይ መነሳቱ ተገቢ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ላይ እያቀረበችው ያለው የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ህጋዊ፣ ታሪካዊ፣ መልክዓ ምድራዊ እውነታን የያዘ ስለመሆኑም አስረድተዋል።
በመሆኑም የባህር በር ጥያቄው ምላሽ እንዲያገኝ መንግስት የመጀመረውን የዲፕሎማሲ ጥረት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አንስተው ሁላችንም ለምላሹ መስራትና መትጋት ይገባናል ሲሉም ተናግረዋል።
በቅርቡ ከኢዜአ ጋር ቆይታ የነበራቸው አንጋፋው ዲፕሎማት አምባሳደር ጥሩነህ ዜና ኢትዮጵያ ከአክሱም ዘመነ መንግስት ጀምሮ በቀይ ባህር አካባቢ ሰላማዊ የንግድ እንቅስቃሴ ስታደርግ የቆየች ሀገር መሆኗን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ላለፉት 30 ዓመታት ከቀይ ባህር ተነጥላ በመቆየቷ የቀይ ባህር አካባቢ ሰላም አጥቶ የአሸባሪዎች መፈንጫ ሆኗል ያሉት አምባሳደሩ ወደ ቀድሞ ቦታዋ ተመልሳ በአካባቢው የሰላም አየር እንዲነፍስ ማድረግ አለባት ብለዋል።
በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያን የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ግልፅነት ሁሉም የሚረዳውና የሚገነዘበው መሆኑን ገልፀው ባለቤትነቱ ጠቀሜታው ለራሷ ብቻም ሳይሆን ለዓለም አቀፍ ሰላም ጭምር መሆኑንም አምባሳደር ጥሩነህ አረጋግጠዋል።