በአፋር ክልል በመደመር እሳቤ እና የውስጥ አቅምን በማጠናከር እየተከናወኑ ባሉ የልማት ሥራዎች እመርታዊ ውጤት እየተመዘገበ ነው - ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ - ኢዜአ አማርኛ
በአፋር ክልል በመደመር እሳቤ እና የውስጥ አቅምን በማጠናከር እየተከናወኑ ባሉ የልማት ሥራዎች እመርታዊ ውጤት እየተመዘገበ ነው - ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 6/2018(ኢዜአ)፦ በአፋር ክልል በመደመር እሳቤ እና የውስጥ አቅምን በማጠናከር እየተከናወኑ ባሉ የልማት ሥራዎች እመርታዊ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ገለጹ።
10ኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም "የከተሞች ዕድገት ለኢትዮጵያ ልህቀት” በሚል መሪ ሀሳብ በአፋር ክልል ሰመራ ሎጊያ ከተማ መካሄድ ጀምሯል፡፡
በመርሀ ግብሩ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ፣ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ፣ የፌደሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ዛህራ ኡመድ፣ የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በመደመር እሳቤ እና የውስጥ አቅምን በማጠናከር በክልሉ ሰፋፊ የልማት ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
ከተሞች በአጭር ጊዜ ውስጥ ለነዋሪዎች ምቹ እንዲሆኑ የሚያስችል ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ በሰመራ ከተማ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት በርካታ ትሩፋቶችን እያስገኘ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በዚህም የንግድ ዘርፉ እንዲነቃቃ ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱንና የአገልግሎት አሰጣጥን ማሳደጉን አብራርተዋል።
በክልሉ እየተከናወኑ ባሉ የልማት ሥራዎች እመርታዊ ለውጥ እየተመዘገበ እንደሚገኝም ነው ርዕሰ መስተዳድሩ ያመላከቱት።
የበረሀማነት ትርክትን ለመቀየር በተከናወኑ ሥራዎች ውጤታማ የግብርና ሥራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል።
የአገልግሎት አሰጣጥ ዲጂታላይዜሽን ሌላኛው በልዩ ትኩረት እየተከናወነ ያለ ስራ መሆኑንም ጨምረው ጠቁመዋል።
በክልሉ ለአልሚዎች ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸው፤ ተጨማሪ እንዲያለሙም ጥሪ አቅርበዋል።