ቀጥታ፡

የተማሪዎች ምገባ መርሀ ግብር  የመጠነ ማቋረጥ ችግርን በመፍታት የተማሪዎች ውጤት እንዲሻሻል አድርጓል

ሀዋሳ፤ ህዳር 6/2018 (ኢዜአ)፦ በሲዳማ ልማት ማህበር የታገዘው የተማሪዎች ምገባ መርሀ ግብር የመጠነ ማቋረጥ ችግርን በመፍታት የተማሪዎች ውጤት እንዲሻሻል ማድረጉን ርዕሰ መምህራንና መምህራን ገለጹ።

በዕውቀት፣ በክህሎትና በመልካም ስነ-ምግባር የታነፀ ዜጋን ለመቅረጽ እንዲሁም ለሀገር ዕድገትና ልማት ትልቁ መሳሪያ ትምህርት መሆኑ ዕሙን ነው።

በአንደኛና ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ትምህርታቸውን በአግባቡ መከታተል እንዲችሉ የትምህርት ቤት ምገባ መርሀ ግብር መጀመር ትልቅ አስተዋጽኦ አለው።

በሲዳማ ክልል ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር እየተከናወኑ የሚገኙ የትምህርት ቤቶች ምገባ መርሃ ግብር የተማሪዎችን ውጤት እያሻሻለ መሆኑ ይገለፃል።

የሲዳማ ልማት ማህበርም በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር የገጠር ቀበሌዎች ቅድሚያ መሰጠት አለባቸው ብሎ በጥናት በለያቸው አራት ትምህርት ቤቶች መርሃ ግብሩን እያካሄደ ይገኛል።

በጉዳዩ ዙሪያ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ ርዕሰ መምህራንና መምህራን እንደገለፁት፤ በማህበሩ የታገዘው የተማሪዎች ምገባ መርሀ ግብር  የመጠነ ማቋረጥ ችግርን በመፍታት የተማሪዎች ውጤት እንዲሻሻል አድርጓል።

የምገባው ተጠቃሚ ከሆኑ ትምህርት ቤቶች መካከል የፊንጫዋ የቅድመ አንደኛና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ሳሰሞ ሰንበቶ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የሲዳማ ልማት ማህበር ካለፈው ዓመት ጀምሮ በትምህርት ቤቱ የተማሪ ምገባ እያደረገ ይገኛል።

ማህበሩ ምገባ መጀመሩን ተከትሎ የተማሪዎች ቁጥር ካለፈው ዓመት አንጻር ከአንድ መቶ በላይ ጭማሪ ማሳየቱንና የተማሪን መጠነ ማርፈድና ማቋረጥ ማስቀረት እንደቻለም ጠቁመዋል።

የትምህርት ቤቱ መምህርት ብዙነሽ ማቲያስ እንዳሉት ምገባ ከተጀመረ ወዲህ ተማሪዎች በሰዓቱ ይመጣሉ በትምህርት አቀባበላቸውም ላይ ከፍተኛ መሻሻልና ለውጥ ማምጣት ችለዋል።

በትምህርት ቤቱ የአራተኛ ክፍል ተማሪ የሆኑት ታሪኬ ዳሮሳ እና ጽዮን ቶርባ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም ተማሪዎች ትምርታቸውን አቋርጠው ወደ ቤታቸው ከመሄድ ባለፈ በተደጋጋሚ ይቀሩ እንደነበር ተናግረዋል።

የምገባ መርሃ ግብሩ ከተጀመረ በኋላ ግን የመማር ተነሳሽነቱ ስለጨመረ ውጤታቸው እንደተሻሻለም አስረድተዋል። 

የሲዳማ ልማት ማህበር ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ወይንሸት መንገሻ እንዳሉት ማህበሩ በትምህርት፣ በጤናና በሌሎች ዘርፎች በክልሉ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።

ማህበሩ በትምህርት ዘርፍ የትምህርት ቤቶች ግንባታ፣ ጥገናና እድሳት እንዲሁም ትምህርት ቤቶችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ የማስተሳሰር ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በምገባ መርሀ ግብር ረገድም በክልሉ ጥናት በማድረግ በአስር ትምህርት ቤቶች ለማስጀመር አቅዶ የተለያዩ አካላትን በማሳተፍ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በአራት ትምህርት ቤቶች በማስጀመር 5 ሺህ የሚሆኑ ተማሪዎችን እየመገበ ነው ብለዋል፡፡

በዚህም በተማሪዎች የትምህርት አቀባበል፣ ትምህርታቸውን በአግባቡ በመከታተል ረገድ ለውጦች መምጣታቸውን አስረድተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም