የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ የብሄራዊ ጥቅምና የሀገር ህልውና ጉዳይ በመሆኑ በሂደቱ የድርሻችንን እንወጣለን - የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ የብሄራዊ ጥቅምና የሀገር ህልውና ጉዳይ በመሆኑ በሂደቱ የድርሻችንን እንወጣለን - የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች
አዳማ፤ ህዳር 6/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ የብሄራዊ ጥቅምና የሀገር ህልውና ጉዳይ በመሆኑ ለምላሹ በሚደረገው ጥረት የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉ የተለያዩ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የቀይ ባህር ጉዳይ ህጋዊ፣ ታሪካዊ፣ መልክዓ ምድራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ እንደሆነ ማንሳታቸው ይታወሳል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የተለያዩ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፤ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ የሀገር ህልውና ጉዳይ እና የሁላችንም የጋራ አጀንዳ ነው ብለዋል።
በዚህ ሂደት ውስጥ የመንግስትን ጠንካራ አቋም ያደነቁት አመራሮቹ ለስኬቱ ሁላችንም አደራ እና ሃላፊነት አለብን ሲሉም ተናግረዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ የብሄራዊ ጥቅምና የሀገር ህልውና ጉዳይ በመሆኑ ለምላሹ በሚደረገው ጥረት የድርሻችንን እንወጣለን ብለዋል።
ከፓርቲዎቹ አመራሮች መካከል የቤንሻንጉል ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ ሊቀመንበር አብዱሰላም ሸንገል፤ የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ በሁሉም መመዘኛዎች ትክክልና ምላሽ ማግኘት ያለበት መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም ፓርቲያቸው የመንግስትን አቋም በመደገፍ ለተግባራዊነቱ የድርሻውን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።
የትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ለብሔራዊ ጥቅም መከበር በጋራ መቆም እንዳለበት እናምናለን ያሉት ሊቀመንበሩ፤ ጥያቄው ምላሽ እንዲያገኝ እጅ ለእጅ ተያይዘን በአንድ ልብ እንሰራለን ብለዋል።
ፓርቲው በቀጣይም ለሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች ስለ ባሕር በር አስፈላጊነትና ብሔራዊ ጥቅም ዙሪያ ግልፅ ግንዛቤና አረዳድ እንዲኖረው የሚጠበቅብትን ይወጣል ነው ያሉት።
የሞቻ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ፕሬዚዳንት አለማየሁ ሻሮ በበኩላቸው፤ የባሕር በር ጥያቄ በግልፅ መነሳቱ ትክክለኛ እና ወቅቱን የጠበቀ በመሆኑ የሚደገፍ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለመልማት፣ ለማደግ፣ የወጪና ገቢ ምርቶችን ለማሳለጥ የግድ የባሕር በር ያስፈልጋታል ያሉት አቶ አለማየሁ፤ ጉዳዩ ምላሽ እስኪያገኝ ድረስ የሚጠበቅባቸው እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።
መንግስት ሰላማዊ እና ዲፕሎማሲያዊ በሆነ አካሄድ የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ እያደረገ ያለው ጥረት በመደገፍ ሁላችንም በጋራ በመቆም መረባረብ አለብን ነው ያሉት።
የባሕር በር ጉዳይ ትውልድና ሀገርን የማስቀጠል የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ለስኬታማነቱ የሚጠበቅብንን እንወጣለን ያሉት ደግሞ የኩሽ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ፓርቲ ፕሬዘዳንት ማንአይቶት በየነ ናቸው።
ፓርቲያቸው የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄው ትክክለኛና ፍትሃዊ መሆኑን አመልክተው፤ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በዚህ ወሳኝ ጉዳይ በጋራ በመቆም መረባረብ አለብን ብለዋል።