የበጋ መስኖ ስንደ ልማት የምርት አቅምንና አማራጭን ከማስፋትም ባለፈ አዲስ የስራ ባህል በመፍጠር ተጠቃሚ አድርጎናል - አርሶ አደሮች - ኢዜአ አማርኛ
የበጋ መስኖ ስንደ ልማት የምርት አቅምንና አማራጭን ከማስፋትም ባለፈ አዲስ የስራ ባህል በመፍጠር ተጠቃሚ አድርጎናል - አርሶ አደሮች
መቱ፤ ኅዳር 6/2018 (ኢዜአ)፦ የበጋ መስኖ ስንደ ልማት የምርት አቅምንና አማራጭን ከማስፋትም ባለፈ አዲስ የስራ ባህል በመፍጠር ተጠቃሚ አድርጎናል ሲሉ የኢሉባቦር ዞን አርሶ አደሮች ተናገሩ።
በኦሮሚያ ክልል ኢሉባቦር ዞን በበጋ መስኖ በ120 ሺህ ሔክታር መሬት ላይ ስንዴ ለማልማት ታቅዶ ወደ ስራ በመግባት የተቀናጀ ስራ በመከናወን ላይ መሆኑንም የኢሉባቦር ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።
በዞኑ እየተከናወነ ያለውን የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እንቅስቃሴ በተመለከተ የኢዜአ ሪፖርተር ተዘዋውሮ አርሶ አደሮችንና የሚመለከታቸውን የስራ ሃላፊዎች አነጋግሯል።
የልማቱ ተሳታፊ አርሶ አደሮቹም መካከል አቶ ከማል አህመድ፤ አቶ ዳኜ ኦላና እና አቶ ሻፊ መዝገቡ፤ በጥቂት አመታት ጊዜ ውስጥ የተጀመረው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ብዙ ጥቅም እያገኘንበት ነው ብለዋል።
የበጋ መስኖ ስንደ ልማት የምርት አቅምንና አማራጭን ከማስፋትም ባለፈ አዲስ የስራ ባህል በመፍጠር ተጠቃሚ አድርጎናል ሲሉም አርሶ አደሮቹ ተናግረዋል።
የበጋ ስንዴ ልማት ላይ ተሰማርተው የሚገኙት አርሶ አደሮቹ ከቅርብ አመታት ወዲህ ዓመቱን ሙሉ የማምረት ባሕል በመላመድ እየሰሩ መሆኑንና በዚህም ውጤታማ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በአካባቢው ያለውን ምቹ እና እምቅ የተፈጥሮ ሃብት በመጠቀም በማልማት እየተጠቀምን እንገኛለን በዚህም ደስተኞች ነን ብለዋል።
በአከባቢያቸው በብዛት ከተለመዱት የበቆሎና ማሽላ እንዲሁም ሌልች ሰብሎች በተጨማሪ በመንግስት የተቀረጸው የመስኖ ስንዴ ልማት ከፍተኛ ጥቅም ያስገኘላቸው መሆኑንም ተናግረዋል።
በዞኑ የያዮ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ በፈቃዱ ኦልጂራ፤ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከ6 ሺህ ሔክታር በላይ ለማልማት ታቅዶ ስራው በመከናወን ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
ለልማቱ የግብአት አቅርቦት በማሟላትና ለአልሚዎቹ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ለውጤታማነቱ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
የኢሉባቦር ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቻላቸው አዱኛ፤ በዞኑ ባለፉት ዓመታት የበጋ ስንዴ ልማት በተለይ የአርሶ አደሩ የስራ ባሕል መሻሻልን ጨምሮ ውጤታማ የማሳ አጠቃቀም እንዲኖር ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
በዘንድሮው የበጋ መስኖ ልማት በዞኑ 120 ሺህ ሔክታር መሬት ላይ ስንዴ የማልማት እቅድ ተይዞ እየተሰራ ስለመሆኑም ገልጸዋል።
በግብርና ልማት ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ አቅርቦቶችን በማሟላት በክላስተር በማረስ ስራው በተጠናከረ መልኩ መቀጠሉን አረጋግጠዋል።