ቀጥታ፡

ባለፉት የለውጥ ዓመታት በከተሞች ብሩህ ተስፋ የፈነጠቁ ስኬቶች ተመዝግበዋል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 6/2018(ኢዜአ)፦ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በከተሞች ብሩህ ተስፋ የፈነጠቁ ትልልቅ ስኬቶች መመዝገባቸውን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ገለጹ፡፡

10ኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም "የከተሞች ዕድገት ለኢትዮጵያ ልህቀት" በሚል መሪ ሀሳብ በአፋር ክልል ሰመራ ሎጊያ ከተማ መካሄድ ጀምሯል፡፡


 

በመርሀ ግብሩ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ፣ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ዛህራ ሁመድ፣ የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች ታድመዋል።

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ፎረሙ እንደ ሀገር የተያዙ የልማት ግቦችና ትልሞች ላይ የጋራ መግባባት የሚፈጠርበት ነው፡፡

ኢትዮጵያ በፈጣን ዕድገት ላይ ካሉ ሀገራት አንዷ መሆኗን ገልጸው፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በከተሞች ብሩህ ተስፋን የፈነጠቁ ትልልቅ ስኬቶች ተመዝግበ ዋል ብለዋል።


 

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የተጀመረው የኮሪደር ልማት ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ ማድረግ መቻሉንም ተናግረዋል።

በኮሪደር ልማት የተከናወኑ ስራዎች ለአፍሪካ በሞዴልነት የሚጠቀሱ መሆናቸውን በማንሳት፤ የተመዘገቡ ስኬቶች እንደተጠበቁ ሆነው ቀሪ ስራዎች ማከናወን ይገባል ብለዋል፡፡

በቀጣይም በመንግስት የተቀመጡ የትኩረት አቅጣጫዎችን በመተግበር ለላቀ ስኬት መስራት እንደሚገባ አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም