በዞኖቹ የምርት አሰባሰብ ተግባር በመካናይዜሽን ታግዞ እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዞኖቹ የምርት አሰባሰብ ተግባር በመካናይዜሽን ታግዞ እየተከናወነ ነው
አዳማ/አምቦ፤ ህዳር 6/2018( ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ እና ምዕራብ ሸዋ ዞኖች የመኸር ምርት ስብሰባ በመካናይዜሽን ታግዞ እየተከናወነ መሆኑን የዞኖቹ ግብርና ጽሕፈት ቤቶች ገለጹ።
የምስራቅ ሸዋ ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ አብነት ዘገየ እንደገለጹት በዞኑ በመኸር አዝመራ ከለማው 500 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ በእስካሁኑ ሂደት 392 ሺህ ሄክታር ላይ የሚገኝ ሰብል በመካናይዜሽንና በሰው ሃይል መሰብሰቡን ገልጸዋል።
የተሰበሰበው ሰብልም ስንዴ፣ ጤፍ፣ ቦሎቄ፣ በቆሎ፣ ማሾና ሌሎች የቅባት እህሎች እንደሚገኙበት አመልክተው በተለይም በኩታ ገጠም የለማው ሰብል በመካናይዜሽን ታግዞ መሰብሰቡን ገልጸዋል።
በዚህም 124 የአጨዳ ኮምባይነሮች፣ 254 የጤፍ መውቅያ ማሽኖች የደረሰውን ሰብል የማጨድና የመውቃት ስራ ማከናወናቸውን ተናግረዋል።
ከተሰበሰበው ሰብልም ከ9 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን ተናግረው ከምርቱም ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታሉ ለውጭ ገቢያ የሚቀርብ ቦሎቄና ማሾ መሆኑንም ገልጸዋል።
በተመሳሳይ በምዕራብ ሸዋ ዞን 138 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የለማ ሰብል መሰብሰቡን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት የአዝእርት ልማት ባለሞያ አቶ በላይ በቀለ ተናግረዋል።
ከተሰበሰበው መሬትም ከ2 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት የተገኘ ሲሆን ሰብሎቹም የብርዕ፣ አገዳ፣ ጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎች መሆናቸውን አንስተዋል።
የተሰበሰበው የሰብል ምርት በመኸር አዝመራው በዘር ከተሸፈነ ከ900 ሺህ ሔክታር መሬት ውስጥ መሆኑንም አስታውሰዋል።
የምርት አሰባሰብ ሂደቱም የሰው ጉልበትን በስፋት በማሳተፍ እና በኮምባይነር በመታገዝ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
አርሶ አደሩ የደረሰ ሰብል በጊዜ እንዲሰበሰብና ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ በግብርና ባለሙያዎች ግንዛቤ እየተሰጠ መሆኑንም አቶ በላይ አስታውቀዋል፡፡