በኦሮሚያ ክልል አርብቶ አደሩ ማህበረሰብ ከእንስሳት እርባታ ጎን ለጎን በግብርና ስራ በመሳተፍ ውጤታማ እየሆነ መጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል አርብቶ አደሩ ማህበረሰብ ከእንስሳት እርባታ ጎን ለጎን በግብርና ስራ በመሳተፍ ውጤታማ እየሆነ መጥቷል
አዲስ አበባ፤ ህዳር 6/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል በቆላማ አካባቢዎች የሚኖረው አርብቶ አደር ማህበረሰብ ከእንስሳት እርባታ ጎን ለጎን በግብርና ስራ በመሳተፍ የምግብ ዋስትናውን እያረጋገጠ መሆኑን የክልሉ መስኖና አርብቶ አደር ልማት ቢሮ ገለጸ።
የክልሉ መስኖና አርብቶ አደር ልማት ቢሮ ኃላፊ ግርማ ረጋሳ ለኢዜአ እንደተናገሩት በክልሉ የአርብቶ አደሩን ማህበረሰብ ህይወት ማሻሻል የሚያስችሉ ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ ይገኛሉ።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት የክልሉ መንግስት በኢኒሼቲቭ መልክ ባከናወናቸው ስራዎች የአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ ከእንስሳት ልማት ጎን ለጎን በግብርና ስራ በመሳተፍ ህይውቱን እያሻሻለ ይገኛል ብለዋል።
መንግስት አርብቶ አደሩ በሚኖርባቸው አካባቢዎች የመሰረተ ልማት ዝርጋታ፣ አነስተኛና መለስተኛ የመስኖ ግድቦች ግንባታ፣ የእንስሳት ጤና አጠባበቅ እና የመኖ ልማት ስራዎች በትኩረት ሲያከናውን መቆየቱን ተናግረዋል።
ከማህበራዊ ልማት አንጻር የትምህርት እና የጤና ተደራሽነት ስራዎች በስፋት መከናወናቸውን ጠቅሰው በተሰሩት ስራዎች
አርብቶ አደሩ በዘመናዊ የግብርና ስራ መሳተፍ መጀመሩን ገልጸዋል።
በተለይም በቦረና ዞን አርብቶ አደሩ ዝናብና መስኖን በመጠቀም ስንዴን እያመረተ ከራሱ ፍጆታ አልፎ ለገበያ እያቀረበ መሆኑን አውስተዋል።
በተመሳሳይም በምስራቅና በምዕራብ ሀረርጌ፣ በባሌና በሌሎች የክልሉ ቆላማ አካባቢዎች የሚገኘው አርብቶ አደር የምግብ ዋስትናውን የሚያረጋግጡ ስራዎች ውስጥ እየተሳተፈ ነው ብለዋል።
በአጠቃላይ በአርብቶ አደር እና ቆላማ አካባቢዎች በዘመናዊ መልኩ በቆሎ፣ ጤፍ፣ ስንዴና አትክልትና ፍራፍሬዎች ልማት እየተከናወነ መሆኑንም አስረድተዋል።
የአርብቶ አደሩ ህይወት በእንስሳት እርባታ ላይ የተመሰረተ እንደመሆኑ መጠን በተለይም በድርቅ ጊዜ የሚያጋጥመውን ጉዳይ ለመቀነስ የእንስሳት ኢንሹራንስ ስርዓት ተዘርግቶ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
በዚህም በአፍሪካ ልማት ባንክና በዓለም ባንክ ድጋፍ በክልሉ በዘጠኝ ዞኖችና በሁሉም ወረዳዎቸ አርብቶ አደሩ ያለውን የእንስሳት ቁጥር በማስመዝገብ ከኢንሹራንስ ስርዓቱ ተጠቃሚ እንዲሆን እየተደረገ መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል።
የአርብቶ አደሩን ማህበረሰብ የቁጠባ ባህል ለማሳደግም የተለያየ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልክተው ተግባሩን በማጠናከር ወደ ተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች እንዲሰማሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር ይሰራል ብለዋል።