ቀጥታ፡

የዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል የማስፋፊያ ግንባታ ተመረቀ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 6/2018(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል የማስፋፊያ ስራ ግንባታ ዛሬ መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአንጋፋው የዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል አዲስ ሆስፒታልን የሚመጣጠን ማስፋፊያ በመገንባት እና ዘመናዊ የህክምና መሳሪያ በማሟላት ስራ መጀመሩን ገልጸዋል።

በሆስፒታሉ የተገነባው የላቀ የሕክምና ማዕከል፣ በ1 ሺህ 800 ካ.ሜ ስፋት ላይ ያረፈ እና ባለ 10 ወለል ህንፃ ሲሆን ለተኝቶ ታካሚዎች አገልግሎት የሚሰጥ 320 አልጋ እንዳለው ጠቁመዋል።

ይህም ላለፉት 91 ዓመታት የነበረውን የዘውዲቱ ሆስፒታል ታካሚ አገልግሎትን በእጥፍ እንደሚያሳድገው አመልክተዋል።

ሆስፒታሉ ለህክምና ባለሙያው እና ለታካሚው በሚመች መልኩ መገንባቱንም የገለጹት ከንቲባዋ።

ማዕከሉ አሁን ላይ የህክምናው ዘርፍ በደረሰበት ዘመናዊ የህክምና መሳሪያዎች የተደራጀ እና የራሱ ኦክስጂን ማምረቻ ጭምር እንደሆነም ተናግረዋል።

ሆስፒታሉ የከተማ አስተዳደሩ አዲስ አበባን የሜዲካል ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ ለጀመረው ሥራ ተደማሪ አቅም እንደሚፈጥር አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም