ኢትዮጵያ በከርሰ እና ገጸ ምድር ማዕድናት ኢንቨስትመንት ዘርፍ መሰማራት የሚያስችሉ ምቹ ህጎች አሏት - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በከርሰ እና ገጸ ምድር ማዕድናት ኢንቨስትመንት ዘርፍ መሰማራት የሚያስችሉ ምቹ ህጎች አሏት
አዲስ አበባ፤ ህዳር 6/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በከርሰ እና ገጸ ምድር ማዕድናት የበለጸገች እንዲሁም በዘርፉ ኢንቨስት ማድረግ የሚያስችሉ ህጎች ያሏት ሀገር መሆኗን ከተለያዩ ሀገራት የመጡ የአራተኛው የማዕድንና ቴክኖሎጂ ኤክስፖ ተሳታፊዎች ገለጹ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ 4ኛውን ዓለም አቀፍ የማዕድንና ቴክኖሎጂ ኤክስፖ ከትናንት በስቲያ መርቀው መክፈታቸው ይታወሳል።
ከህዳር 4 እስከ 7 ቀን 2018 ዓ.ም በሚካሔደው ዓለም አቀፍ የማዕድንና ቴክኖሎጂ ኤክስፖ የሀገር ውስጥና የውጭ አልሚዎች፣ አምራቾችና ምሁራን እየተሳተፉ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያነጋገራቸው የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት የኤስፖው ተሳታፊ አልሚዎች፤ ኢትዮጵያ በተለያዩ የማዕድን ሃብቶች የበለጸገች መሆኗን ገልጸዋል፡፡
በወርቅ ማጣራት ዘርፍ የተሰማራው የሳዑዲ አረቢያው ዩናይትድ ግሎባል ማይኒንግ ካምፓኒ ዋና ሥራ አስኪያጅና የጂኦሎጂካል አማካሪ ሳላህ ዳህላዊ፤ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በወርቅ ማጣራት ዘርፍ ለመሰማራት ፈቃድ አግኝቶ ስራ ለመጀመር የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
በወርቅ ማጣራት ሥራ ኢንቨስትመንት ለመሰማራት ወደ ኢትዮጵያ የመጡት በሳዑዲ አረቢያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባቀረበላቸው ግብዣ መሰረተ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣም ሀገሪቱ ወርቅን ጨምሮ በተለያዩ የከርሰ እና ገጸ ምድር ማዕድናት ጸጋ የተቸረችና በዘርፉ ለመሰማራት የተቀመጡ ህጎች ኢንቨስትመንትን የሚያበረታቱ ሆነው እንዳገኟቸው ተናግረዋል፡፡
ስራቸውን ለመጀመር እንቅስቃሴ ከጀመሩ በኋላም መንግስት የተለያዩ ድጋፎችንና ማበረታቻዎችን እያደረገላቸው እንደሚገኝ ጠቁመው፤ ለዚህም ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ምስጋና ይገባል ብለዋል።
የዳንጎቴ ኢትዮጵያ ሲሚንቶ ፋብሪካ ሲነየር ጂኦሎጂስት ስንታየሁ ዘውዴ፤ ዳንጎቴ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በዓመት 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቶን ሲሚኒቶ እያመረተ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በርካታ ለሲሚንቶ ምርት ግብዓት የሚሆኑ ማዕድናት ክምችት ያላት ሀገር መሆኗን በመጥቀስ፤ በቀጣይ የካምፓኒውን የማምረት አቅም በእጥፍ ለማሳደግ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ለዚህ ደግሞ የማዕድን ዘርፉን እንቅስቃሴ ማሳለጥ የሚያስችል ፖሊሲዎችን ህጎች ምቹ መሆናቸወን ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የጣሊያን ኤምባሲ የንግድ ኮሚሽነር ክላውዲኦ ፓስኳሉሲ በበኩላቸው፤ የጣሊያን መንግስት "ማቴኢ ፕላን" የተባለ የአፍሪካ ኢንቨስትመንት እቅድ እንዳለው ተናግረዋል፡፡
በዚህ የኢንቨስትመንት እቅድ ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ምርጫ ሆና መቀመጧን ገልጸው፤ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርሙና የኢንቨስትመንት ህጎች ምቹነት ኢትዮጵያን ተመራጭ አድርገዋታል ብለዋል፡፡