በጋምቤላ ክልል የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ ይከበራል - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ ይከበራል
ጋምቤላ፤ ህዳር 6/2018(ኢዜአ)፡- በጋምቤላ ክልል የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ በተለያዩ ሁነቶች ለማክበር ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ መሰረት ማቲዎስ ገለጹ።
አፈ-ጉባዔዋ አከባበሩን አስመልክተው እንዳስታወቁት፤ 20ኛው የኢትዮጵያ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በክልል ደረጃ በአኝዋሃ ዞን ዲማ ወረዳ አስተናጋጅነት በድምቀት ይከበራል።
ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ ለማክበር አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል።
በዓሉ በክልሉ የሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦች በባህላዊ እሴቶቻቸው የሚያሳዩበትና ይህም የቱሪዝም ልማቱን ለማጎልበት በሚደረገው ጥረት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
በዓሉ በክልሉ በሚገኙ የአስተዳደር እርከኖችና አደረጃጀቶች በፌዴራሊዝም ሥርዓትና በህገ መንግስት አስተምሮን ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ የውይይት መድረኮች እየተካሄዱ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይም በትምህርት ቤቶች በጥያቄና መልስ እና በስፖርታዊ ውድድሮች እንዲሁም በሌሎች ሁነቶች በዓሉ እንደሚከበርም አንስተዋል።
አካባበሩ በክልል ደረጃ እስከ ህዳር 20/2018ዓ.ም በማጠናቀቅ በሀገር አቀፍ ደረጃ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ በሚከበረው የኢትዮጵያ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ላይ ለመታደም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ለኢዜአ ጨምረው ገልጸዋል።