በዘመናዊ መልኩ የተገነባው ትምህርት ቤት ምቹ የመማር ማስተማር ከባቢ ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
በዘመናዊ መልኩ የተገነባው ትምህርት ቤት ምቹ የመማር ማስተማር ከባቢ ፈጥሯል
አዲስ አበባ፤ ህዳር 6/2018(ኢዜአ)፦ ትምህርት ቤቱ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ በመገንባቱ ምቹ የመማር ማስተማር ከባቢ መፍጠሩን የሐይቅ ቁጥር አንድ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራንና ተማሪዎች ገለጹ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በደቡብ ወሎ ዞን ሐይቅ ከተማ በበላይነህ ክንዴ ፋውንዴሽን የተገነባውን ትምህርት ቤት መርቀዋል፡፡
የትምህርት ቤቱ መገንባት ተማሪዎች ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኙ እንደሚያስችልም ተጠቁሟል፡፡
የትምህርት ቤቱ መምህራን አርባሽኩር በቀለና መሐመድ ኢማምቡላል ቀደም ሲል ምቹ ባልሆኑ የመማሪያ ክፍሎች ሲያስተምሩ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
ምቹ ሁኔታ ባለመኖሩ ተማሪዎች ጥራት ያለው ትምህርት እንዳያገኙ ከማድረጉም በላይ፣ መምህራን ዕውቀትን በአግባቡ ተደራሽ ለማድረግ ምቹ እንዳልነበር ገልጸዋል።
አሁን ግን አዲሱ ትምህርት ቤት ወደ አገልግሎት መግባቱ ተማሪዎች ምቹ በሆኑ ክፍሎች ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኙ አስችሏል ብለዋል።
መምህራኑ እጅግ ደስተኛ ሆነው ዕውቀታቸውን ለተማሪዎች በማስተላለፍ ላይ መሆናቸውን ገልጸው፣ ትምህርት ቤቱን የገነቡ አካላትን አመስግነዋል።
ተማሪ ሐምዛ መሐመድ እና ሰላም ተስፋዬ በሰጡት አስተያየት፤ ቀደም ሲል ምቹ ወንበር ያልነበራቸውና በጠባብ የመማሪያ ክፍሎች በርካታ ተማሪዎች አንድ ላይ ይማሩ እንደነበር አስታውሰዋል።
አሁን ግን አዲሱ የመማሪያ ክፍል ምቹ ወንበርና ጠረጴዛ የተሟላለት እንዲሁም ከጽዳት አኳያም ንጹህ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከአሁን በኋላ መደበኛ ትምህርታቸውን በጥሩ ሁኔታ በመከታተል ትልቅ ደረጃ ለመድረስ ጠንክረው እንደሚማሩ ገልጸዋል።
የቤተ-መጽሐፍት ባለሙያዋ ምሥራቅ ጀማል በበኩሏ አዲስ የተገነባው ቤተ-መጽሐፍት መጻሕፍት የተሟሉለትና ሰፊ መሆኑን ተናግራለች።
ይህም በርካታ ተማሪዎች የሚፈልጉትን የትምህርት ዓይነት በምቹ ሁኔታ ለማንበብ እንደሚረዳቸው ገልጻለች።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ከሐይቅ የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት ጎን ለጎን ባለ ሀብቱ በላይነህ ክንዴ ያስገነቡትን ገበታ ለትውልድ ሐይቅ ቁጥር 1 አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመልክተናል ብለዋል፡፡
ከአብርሆት ቤተ መጻሕፍት ያገኙትን 4250 መጻሕፍት ለትምህርት ቤቱ ቤተ መጻሕፍት ማስረከባቸውንም ገልጸው ይህ ሁሉ የልማቱና የሰላሙ ትሩፋት ነው ማለታቸውም ይታወሳል።