የዘንድሮው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ለማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ልዩ ዕድል ይዞ መጥቷል - የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋጤ ሰርሞሎ - ኢዜአ አማርኛ
የዘንድሮው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ለማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ልዩ ዕድል ይዞ መጥቷል - የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋጤ ሰርሞሎ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 6/2018(ኢዜአ)፦ የዘንድሮው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ለማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ይዞት የመጣውን ልዩ ዕድል በአግባቡ በመጠቀም በርካታ የመሰረተ ልማት ስራዎች መሰራታቸውን የክልሉ አፈ ጉባኤ ፋጤ ሰርሞሎ ገለጹ።
20ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን አከባበርን አስመልክቶ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋጤ ሰርሞሎ መግለጫ ሰጥተዋል።
አፈ ጉባኤዋ በመግለጫቸው ለበዓሉ ኢትዮጵያን በሚመጥን መልኩ ከፍተኛ ዝግጅት ሲደረግ ቆይቷል ብለዋል።
የዘንድሮው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ባስመረቅንበት ማግስት ትልልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ወደ ስራ ለማስገባት መሰረት የተጣለበት ወቅት ላይ በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል ነው ያሉት።
ክልሉ ከተመሰረተ አጭር ጊዜ ቢሆነውም ይህን ሀገራዊ ሁነት ለማስተናገድ ሃላፊነት ወስዶ በቁርጠኝነት ወደ ስራ መግባቱንም አፈ ጉባኤዋ ጠቁመዋል።
ለአብነትም በአጭር ጊዜ ውስጥ ለበዓሉ ማክበሪያ የሚሆን አዳራሽና ልዩ ልዩ መሰረተ ልማቶች መገንባታቸውን ተናግረዋል።
በዓሉ ለማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ልዩ ዕድል ይዞ መጥቷል መምጣቱን ጠቅሰው እድሎችን በእግባቡ በመጠቀም በርካታ የመሰረተ ልማት ስራዎች መሰራታቸውን አንስተዋል።
የክልሉ ህዝብም እንግዶችን ተቀብሎ ለማስተናገድ በሁለንተናዊ መልኩ ዝግጁ ሆኖ በመጠባበቅ ለይ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በክልሉ በርካታ የኮሪደር ልማት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸው በመጠናቀቅ ላይ ያሉ የኮሪደር ልማት ስራዎችን ከብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ጋር ተያይዞ ለማስመረቅ ዝግጅት ላይ እንደሚገኝም አንስተዋል።
20ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ’’ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለህብረብሄራዊ አንድነት’’ በሚል መሪ ሀሳብ በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አስተናጋጅነት በሆሳዕና ከተማ ይከበራል።