ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የምታዘጋጀው የሴካፋ ዞን ከ17 ዓመት በታች አፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ  ይጀመራል ዛሬ ይጀመራል   

አዲስ አበባ፤ ህዳር 6/2018(ኢዜአ)፦ 16ኛው ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ዛሬ ይጀመራል። 

የአፍሪካ ዋንጫው እ.አ.አ በ2026 በሞሮኮ አስተናጋጅነት ይከናወናል። 

በውድድሩ ላይ የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ማህበራት ምክር ቤት(ሴካፋ) ዞንን ወክለው የሚሳተፉ ሁለት ሀገራት የሚለዩበት የማጣሪያ ውድድር በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳል።

ሴካፋ የማጣሪያ ውድድሩ የምድብ ድልድል ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት በዩጋንዳ ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው።

በምድብ አንድ አዘጋጇ ኢትዮጵያ ከሶማሊያ፣ ኬንያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ሩዋንዳ ጋር ተደልድላለች። 

ዩጋንዳ፣ ታንዛንያ፣ ጅቡቲ፣ ሱዳን እና ብሩንዲ በምድብ ሁለት የተደለደሉ ሀገራት ናቸው። 

ውድድሩ በአበበ ቢቂላ እና ድሬዳዋ ኢንተርናሽናል ስታዲየሞች ይካሄዳል።


 

ቡድኖቹ አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ የእድሜ ተገቢነት (MRI) ምርመራ በማከናወን ዩጋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ታንዛንያ፣ ሱዳን እና ጅቡቲ የምድብ ጨዋታቸውን ወደ ሚያደርጉበት ድሬዳዋ ያመሩ ሲሆን ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ እና ሩዋንዳ ደግሞ የምድብ ጨዋታቸውን አዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ላይ የሚያከናውኑ ይሆናል።

ዛሬ አዘጋጇ ኢትዮጵያ ከሩዋንዳ ከቀኑ 10 ሰዓት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይጫወታሉ።

ሶማሊያ ከደቡብ ሱዳን ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ የሚያደርጉት ጨዋታ የመክፈቻ መርሃ ግብር ይሆናል።

በድሬዳዋ ኢንተርናሽናል ስታዲየም ታንዛንያ ከሱዳን ከቀኑ 11 ሰዓት፣ ብሩንዲ ከዩጋንዳ ከምሽቱ 2 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። 

የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የሴካፋ ዞን ከ17 ዓመት በታች አፍሪካ ዋንጫ የማጣርያ ውድድር ዝግጅቱን በአዲስ አበባ ሲያደርግ ቆይቷል። 

ብሄራዊ ቡድኑ የሚሰለጥነው በአሜሪካዊው ቤንጃሚን ዚመር ነው።

ተጫዋቾቹ የተመለመሉት ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2026 የሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ለማስተናገድ ያቀረበችው ጥያቄ አካል የሆነው የ"Road to 2029" ፕሮጀክት የ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ካምፒንግ መሆኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። 

የሴካፋ ዞን ማጣሪያ እስከ ህዳር 23 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል። 

በማጣሪያው ለፍጻሜ የሚያልፉት ሁለት ሀገራት የሴካፋ ዞንን ወክለው ለአፍሪካ ዋንጫ ያልፋሉ። 

እ.አ.አ በ2026 በሚካሄደው 16ኛው ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጇ ሞሮኮን ጨምሮ 16 ሀገራት ይሳተፋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም