ቀጥታ፡

 የኢትዮጵያ የኮፕ 32 አዘጋጅነት

ለረጅም አስርት ዓመታት ኢትዮጵያ የአፍሪካ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ምሰሶ ሆና ቆማለች። በሀገራት መካከል የግንኙነት ድልድል እና የአንድነት መልዕክተኛ መሆን ችለላች።

ከምስረታው አንስቶ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ ናት። የአፍሪካ መዲና በመባል የምትጠራው አዲስ አበባ በርካታ ድርድሮች፣ የሰላም ውይይቶች እና አህጉራዊ ውሳኔዎች የተላለፈባቸው ሁነቶች ተስተናግደውባታል። ውሳኔዎቹ የአፍሪካ ቀጣና ፖለቲካ እና የልማት ጉዞ ላይ አሻራቸውን ያሳረፉ ናቸው።

የኢትዮጵያ የመሪነት ሚና ከዲፕሎማሲውም የተሻገረ ነው። ሀገሪቷ የገባችውን ቃል ከተግባር ጋር በማጣጣም በአየር ንብረት ለውጥ ላይ እርምጃ በመውሰድ የሚለኩ ውጤቶችን እያስመዘገብች ትገኛለች። 

የተራቆቱ መሬቶች ወደ ነባር ይዞታቸው እንዲመለሱ በማድረግ እና የታዳሽ ኃይል አማራጮቿን በማስፋት ለአረንጓዴ ልማት እና እድገት ያላትን ቁርጠኝነት አሳይታለች። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የተጀመረው አረንጓዴ አሻራ ሚሊዮኖችን ከዳር እስከ ዳር በማነቃነቅ ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ከችግር ተናገሪነት ወደ ተጨባጭ መፍትሄ አመንጪነት ሽግግር በማድረግ በአፍሪካ እና በዓለም ደረጃ ምሳሌ የሚሆን ተግባር አከናውናለች። 

ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ያስመዘገበቻቸው ስኬቶች በዓለም ደረጃ ያላትን ተአማኒነት እና ተቀባይነት እንዲያድግ አድርጎታል። ኢትዮጵያ በከባቢ አየር ጥበቃ ቁርጠኝነት እና አቅምን በማጣመር ለውጥ አምጥታለች። 

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያገኘችው እምነት እና የመሪነት ሚና ውጤት የሚያሳይ ተጨማሪ ሃላፊነት ከሰሞኑ ከብራዚል የደን ከተማ ቤለም ተሰምቷል። 30ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 30) በቤለም እየተካሄደ ይገኛል። የዓለም ሀገራት በአንገብጋቢ የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳዮች እና ቀጣይ የመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ እየመከሩ ይገኛል። 

በጉባኤው ላይ እየተሳተፈች የምትገኘው ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2027 የሚካሄደውን 32ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ለማስተናገድ ይፋዊ ጥያቄ አቅርባለች። 

በብራዚል የኢትዮጵያ አምባሳደር ልዑልሰገድ ዓለም ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የገቡትን ቃል በተግባር ለመቀየር ቁርጠኝነት ባነሳቸው ወቅት ኢትዮጵያ ለሌሎች ምሳሌ የሚሆን ተግባር መፈጸሟን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን በማዘጋጀት የረጅም ጊዜ ልምድ እንዳላት ገልጸው የዳበረ የትራንስፖርት አገልግሎት ከብዙ የዲፕሎማሲ ተቋማት መቀመጫነት ጋር ሲደመር የዝግጁነት አቅሟን በላቀ ሁኔታ እንደሚያሳድገው አመልክተዋል።  

ኢትዮጵያ 32ኛውን የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን ለማዘጋጀት ኢትዮጵያ ልምዱም አቅሙም እንዳላት ገልጸው፣ ሀገራት ድጋፍ እንዲሰጡ ጠይቀዋል። ናይጄሪያም ጉባኤውን ለማስተናገድ ጥያቄ አቅርባ ነበር። 

የኢትዮጵያ የኮፕ 32 የማስተናገድ ፍላጎት ከአፍሪካ ሀገራት ሙሉ ድጋፍ አግኝቷል። የወቅቱ የአፍሪካ የአየር ንብረት ተደራዳሪዎች ቡድን ሊቀመንበር የሆነችው ታንዛንያ የኢትዮጵያ ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱን ገልጻለች።

የአፍሪካውያን ውሳኔ ከቃል ባሻገር ኢትዮጵያ የአህጉሪቷን የአየር ንብረት የቅድሚያ ትኩረቶች የማራመድ እና የመወከል አቅም አላት ብለው ይሁንታ የሰጡበት ነው። ይህ ጠንካራ እምነት ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ሁሉን አፍሪካውያን ያሳተፈ ውይይት እንዲደረግ እና አህጉሪቷን ያማከለ ውሳኔዎች በዓለም መድረክ እንዲተላለፍ እያደረገች ያለውን ጥረት ይበልጥ ውጤታማ የሚያደርግም ነው። 

በብራዚል የኢትዮጵያ አምባሳደር ልዑልሰገድ ታደሰ አፍሪካውያን ኢትዮጵያ ኮፕ 32ን እንድታስናግድ ድጋፍ በመስጠታቸው አመስግነው፤ ጉባኤውን በተሳካ ሁኔታ ለማስተናገድ አበክራ እንደምትሰራ ተናግረዋል። 

በቅርቡ በአዲስ አበባ የተካሄደው ሁለተኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤ ኢትዮጵያ መሰል አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ሁነቶችን በብቃት ማስተናገድ እንደምትችል የሚያመላክት ነው ብለዋል። 

አዲስ አበባ እንግዶቿን በሚመጥን ደረጃ ጉባዔውን ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኗን ያረጋገጡት አምባሳደሩ፥ ለኢትዮጵያ ጥያቄ ሌሎች ሀገራትም ድጋፍ እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ የኮፕ 32ን ለማስተናገድ መመረጧ በድንገት የመጣ ጉዳይ አይደለም። በተግባር የተረጋገጥ የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል የመሪነት ሚና፣ አረንጓዴ እና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት እያከናወነች ያለቻቸው ስራዎች እና የፖለቲካ ቁርጠኝነቷ፣ የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ድምጽ እና ምልክት መሆኗ ከቃል ባለፈ በተጨበጠ ስራ መታየቱ፣ ዓለም አቀፍ ሁነቶችን የማስተናገድ ውጤታማነቷ እና የዲፕሎማሲ ተሰሚነቷ ድምር ውጤቶች እንጂ። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ኢትዮጵያ ኮፕ 32ን እንድታስተናግድ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ትልቅ ኃላፊነት ስለሰጠን ክብር ይሰማናል ብለዋል።

አፍሪካ በ2025 በተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ኮንፈረንስ (COP 30) ላይ በብራዚል በአንድ ድምጽ ተናግራለች፤ ዓለምም አዳምጧል ብለዋል።
እንዲሁም ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ በ2027 በአዲስ አበባ COP 32ን ለማስተናገድ ያቀረበችውን ጥያቄ ሙሉ በሙሉ ለደገፉ የአፍሪካ ሀገራት ተወካዮች ምሥጋና አቅርበዋል።

በሰው ልጆች ኑሮ በጣም አንገብጋቢ ከሆኑት ተግዳሮቶች መካከል አንዱን ለመቅረፍ እንዲቻል የጋራ ጥረቶችን ለመምራት ዕድሉን ስላገኘንም አመሥጋኞች ነን ብለዋል። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይህን ትልቅ ኃላፊነት ስለሰጠንም ክብር ይሰማናል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ይህ ዕውቅና ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ላይ ያላትን ቁርጠኛ ርምጃ፣ አመራር ብሎም ዋና ዋና ዓለም አቀፍ ዝግጅቶችን የማስተናገድ የዳበረ ዐቅም ያሳያል ሲሉም በአጽንኦት ገልጸዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ በምታስተናግደው የኮፕ 32 መድረክ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የጋራ ርምጃን የሚያበረታታ ጠንካራ እና ትርጉም ያለው ውጤት ለማምጣት ሙሉ በሙሉ ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ ኮፕ 32ን ማዘጋጀቷ በዓለም አቀፍ እና ቀጣናዊ መድረኮች ኢትዮጵያ ያላትን የአየር ንብረት የመሪነት ሚና የበለጠ ያሳድጋል። የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ስራ የሚያስፈልጋትን ፋይናንስ ለማግኘት እና ዓለም አቀፍ አጋርነትን ለማጠናከር መልካም አጋጣሚን ይፈጥርላታል። 

በሺህዎች የሚቆጠሩ የጉባኤው ተሳታፊዎች የቱሪዝም መስህቧቿንና መዳረሻዎቿን ሲጎበኙ ከዘርፉ የሚያገኘው ገቢ ያድጋል ይህም ኢኮኖሚውን በመደገፍ ቁልፍ ሚና ይጫወታል።

በአፍሪካ ዲፕሎማሲ ውስጥ ያላትን ተጽእኖ ፈጣሪን ጉባኤው በማስተናገድ በኩል ጉልህ አበርክቶ የሚኖረው ሲሆን ዘላቂ የሆነ የከባቢ አየር ትብብርን ለመፍጠር ያስችላል። 

ለኢትዮጵያ ኮፕ 32ን ማስተናገድ ከክብር ባሻገር ኢትዮጵያ ለአፍሪካ እና ሰው ለሚኖርባት ምድር ጥበቃ ያላትን ቁርጠኝነት በተግባር የምታሳይበት ይሆናል።

ኢትዮጵያ ጠንካራ የከባቢ አየር ጥበቃ ኢኒሼቲቮች፣ የማይበገር ዲፕሎማሲ እና የነገ አረንጓዴ እድገት ህልሟ ከጉባኤው ጋር ተዳምረው የተፈጥሮ ጠበቃነቷን እና የዓለም ትብብር ተምሳሌትና መሪነቷን የበለጠ ያሳድጉታል። 

ኢትዮጵያ እና ህዝቧቿ ከመቼውም ጊዜ በላይ የአየር ንብረት የረጅም ጊዜ ፈተናዎች እንዲፈቱ ከአፍሪካ ብሎም ከመላው ዓለም ጋር ለመፍታት ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ እና ቁርጠኛ ናት። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም