ቀጥታ፡

ኢንተርፕርነርሽፕ ኢትዮጵያ ያላትን ዕምቅ አቅም ጥቅም ላይ እንድታውል እያደረገ ነው - ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 5/2018(ኢዜአ)፦ ኢንተርፕርነርሽፕ ኢትዮጵያ ያላትን ዕምቅ አቅም ጥቅም ላይ እንድታውል እያደረገ መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።

ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል "በጋራ እንገንባ" በሚል መሪ ሀሳብ ከህዳር 8 እስከ 18 ቀን 2018 ዓ.ም የሚካሄደውን ዓለም አቀፍ የኢንተርፕርነርሽፕ ሳምንት በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም መንግስት የኢንተርፕርነርሽፕ ሥራን ለማስፋት ቁርጠኛ በመሆኑ ዘርፉ ትልቅ ደረጃ ላይ ደርሷል ብለዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አመራር የማይበገር ሀገር ለመገንባት ለዘርፉ ትኩረት በመስጠቱ ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።

ኢንተርፕርነርሽፕ ከሥራ ፈጠራና የሰው ሀይል ልማት ባለፈ ሀገር የመገንባት ጉዳይ መሆኑንም አንስተዋል።

የመደመር መንግሥት ዕሳቤ ተቋማት እሴት መፍጠር እንዳለባቸው ያምናል ያሉት ሚኒስትሯ፤ በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የተመዘገበው ለውጥ ማሳያ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ የኢንተርፕርነርሽፕ ዘርፉን ማገዝ እንደሚገባ በመጠቆም፤ የዘንድሮው የኢንተርፕርነርሽፕ ሳምንት እንደሀገር ከያዝነው እሳቤ ጋር ይጣጣማል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ጉዞ ተጀምሯል ያሉት ሚኒስትሯ፣ በእስከ አሁን የተመዘገቡና የታዩ ለውጦች እንደምንችል ማሳያ ናቸው ነው ያሉት።

ጉዟችን የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና እስከሚረጋገጥ በመሆኑ ረጅሙን ጉዞ በፈጠራና ኢንተርፕርነርሽፕ ማገዝ ይገባል ብለዋል።

ዓለም አቀፉ የኢንተርፕርነርሽፕ ሳምንት ከህዳር 8 ቀን ጀምሮ ለአስር ተከታታይ ቀናት በተለያዩ ሁነቶች እንደሚካሄድም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በኢንተርፕርነርሽፕ ግዙፍ መሆኗን በማንሳት ይህም በዘርፉ በዓለም ሥነ ምህዳር ኢትዮጵያ የሚታይ ስራ እንዳላት ያመለክታል ብለዋል።

መርሀ ግብሩ በዘርፋ ከኢትዮጵያ ጋር አብረው መስራት የሚፈልጉ ተቋማትን የምናገኝበት ይሆናል ያሉ ሲሆን የስታርታፕ አዋጁን ጨምሮ የተወሰዱ እርምጃዎች መንግስት ለዘርፉ እድገት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ያመላክታል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም