በሶማሌ ክልል የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን ህብረ ብሄራዊ አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ ይከበራል - ኢዜአ አማርኛ
በሶማሌ ክልል የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን ህብረ ብሄራዊ አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ ይከበራል
ጅግጅጋ፤ ህዳር 5/2018(ኢዜአ)፦ በሶማሌ ክልል የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ህብረ ብሄራዊ አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ እንደሚከበር ተገለጸ።
በክልሉ አከባበሩን በተመለከተ የዝግጅቱ አብይ ኮሚቴ በአከባበሩ ዙሪያ ዛሬ ተወያይቷል።
የሶማሌ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ መሀመድ አዳን እንደገለጹት በክልሉ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ህብረ ብሄራዊ አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ ይከበራል።
በክልሉ በዓሉ በወረዳ፣ በዞንና በከተማ አስተዳደሮች ከዛሬ ጀምሮ እስከ ህዳር 15 ቀን 2018 ዓ.ም በደም ልገሳ፣ በንግድና ባዛር፣ በችግኝ ተከላ፣ በስፖርታዊ ውድድሮች፣ በፓናል ውይይት፣ አረጋውያንን በመደገፍና በሌሎች ዝግጅቶች እንደሚከበር ተናግረዋል።
በክልል ደረጃ ህዳር 18 ቀን 2018 ዓ.ም በጅግጅጋ ከተማ የበዓሉ ማጠቃላይ ፕሮግራም እንደሚካሄድም አስታውቀዋል።