በክልሉ የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ የተማሪዎችን መጠነ ማለፍ ለማሳደግ በትኩረት ተሰርቷል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ የተማሪዎችን መጠነ ማለፍ ለማሳደግ በትኩረት ተሰርቷል
ቡታጅራ፤ ህዳር 5/2018(ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ የተማሪዎችን መጠነ ማለፍ ለማሳደግ በትኩረት መሰራቱን የክልል ትምህርት ቢሮ ገልጿል።
የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር በበኩሉ ለትምህርት ጥራትና ለመምህራን መብት መከበር የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን አስታውቋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መምህራን ማህበር 2ኛ ዙር የትምህርት ጥራት ኮንፍረንስና የመምህራን ቀን በቡታጀራ ከተማ ተካሂዷል።
በዚሁ ወቅት የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አስከብር ወልዴ በክልሉ የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ የተማሪዎችን መጠነ ማለፍ ለማሳደግ ተሰርቷል ብለዋል።
መምህራን በስነ-ምግባር የታነፀ፣ ብቁና ሀገር ወዳድ ዜጋ ለማፍራት የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመትት የመምህራንን አቅም በማጎልበት በኩል ሰፋፊ ስራዎች መከናወናቸውንና በዚህም ስኬቶች መመዝገባቸውን ጠቁመዋል።
መምህራን የሚገባቸውን ጥቅማ ጥቅም እንዲያገኙ በተሰራው ስራም ውጤት መገኘቱን ምክትል ቢሮ ሀላፊው ተናግረዋል።
በመድረኩ የተገኙት የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት ዮሃንስ በንቲ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በእውቀት እና በስነ ምግባር የታነጸ ትውልድ ለመቅረፅ በሚደረገው ጥረት የመምህራን አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ለስኬታማነቱም ማህበሩ የመምህራንን እውቀትና ክህሎት በማጎልበት ለትምህርት ጥራትና መብታቸውን ለማስከበር የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን አንስተዋል።
ማህበሩ የመምህራንን መብት በማስከበር እንዲሁም ዕውቀትና ክህሎታቸውን እንዲያሳድጉ የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት በርታ ያረቢ ናቸው።
ማህበሩ የተጀመረውን የትምህርት ሪፎርም ውጤታማ ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝም አክለዋል፡፡
ለትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ውጤታማ አስተዋፅኦ ላበረከቱ መምህራን፣ ወላጆች፣ ተማሪዎችና ባለድርሻ አካላት እውቅና በየጊዜው እየተሰጠ መሆኑንም ተናግረዋል።
በኮንፍረንሱ በክልሉ በትምህርት ጥራት እና ተደራሽነት ላይ ያተኮረ ጥናት ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ሲሆን የተሻለ አፈፈፃፀም ያስመዘገቡ መምህራን፣ ውጤታማ ተማሪዎችና ወላጆች ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።