የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን መከበር ለጋራ ልማትና ዕድገት በአንድነት እንድንተጋ መነሳሳትን ፈጥሯል - የመንግስት ሰራተኞች - ኢዜአ አማርኛ
የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን መከበር ለጋራ ልማትና ዕድገት በአንድነት እንድንተጋ መነሳሳትን ፈጥሯል - የመንግስት ሰራተኞች
ወልዲያ፤ ህዳር 5/2018(ኢዜአ)፦ የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን መከበር ለጋራ ልማትና ዕድገት ሁላችንም በህብረ ብሔራዊ አንድነት እንድንተጋ መነሳሳት ፈጥሮልናል ሲሉ የወልዲያ ከተማና የሰሜን ወሎ ዞን የመንግስት ሠራተኞች ተናገሩ።
በአገራችን የሚከበረው 20ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን "ብሄራዊ መግባባት ለህብረ-ብሄራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ በወልዲያ ከተማ በፓናል ውይይት ተከብሯል።
ውይይቱ ላይ የተሳተፉ የመንግስት ሠራተኞች እንዳሉት፤ የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን መከበር ለጋራ ልማትና ዕድገት በህብረ ብሔራዊ አንድነት እንድንተጋ መነሳሳትን ፈጥሯል።
ከተሳተፊዎቹ መካከል አቶ ታምራት ወራሴ በዓሉ ስለ ህገ መንግስት፣ ዴሞክራሲና የፌደራል ስርዓት ፋይዳ ዙሪያ እውቀት እንድንጨብጥ አስችሎናል ብለዋል።
የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦች አገር የሆነችው ኢትዮጵያ የህዝቦቿ አንድነት ዛሬም በእኛ ዘመን ተጠናክሮ እንዲቀጥል የጋራ ትርክት ላይ በማተኮር መስራት እንደሚገባም አመልክተዋል።
ነጠላ ትርክትን በማስወገድ ለጋራ ልማትና ዕድገት በአንድነት ልንተጋ ይገባል ያሉት ደግሞ ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ጀማል ሙሐመድ ናቸው።
የህገ-መንግስቱ መልካም ትሩፋቶች ለጋራ ተጠቃሚነታችን ፈር ቀዳጅ በመሆናቸው ተጠብቆ ለዘላቂ ሰላምና ልማት ማዋል ይገባል ብለዋል።
የሰሜን ወሎ ዞን ፍትህ መምሪያ ኃላፊና ውይይቱን የመሩት አቶ ፍስሃ መንግስቴ በበኩላቸው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን ቀንን ስናከብር ለህዝቦች ሠላም፣ ፍቅርና አንድነት በመስራት መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በዓሉን ስናከብር በህብረ ብሔራዊ አንድነት ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ሃገረ መንግስትን እውን ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ሊሆን ይገባልም ብለዋል።
የዘንድሮውን በዓል ለየት የሚያደርገው የህዳሴ ግድባችን ባስመረቅንበት ማግስት የሚከበር በመሆኑ ደስታችንን እጥፍ ድርብ ያደርገዋል ያሉት ደግሞ የወልዲያ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባዔ አቶ ኢትዮጲስ አያሌው ናቸው።
በዓሉን ስናከብርም በህብረ ብሔራዊ አንድነት የተገነባችውን ኢትዮጵያ ወደፊት ለማሻገር ቁርጠኛነታችንን በማረጋገጥ መሆን አለበት ብለዋል።
በመድረኩ ላይም የወልዲያ ከተማ አስተዳደር፣ የሰሜን ወሎ ዞን የመንግስት ሠራተኞችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት "ዴሞክራሲና የኢትዮጵያ ፌደራል ስርዓት" በሚል ርእስ ውይይት አካሄደዋል።