ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የጋራ ርምጃን የሚያበረታታ ውጤት ለማምጣት ቁርጠኛ ናት - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 5/2018 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ በኮፕ 32 መድረክ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የጋራ ርምጃን የሚያበረታታ ጠንካራ እና ትርጉም ያለው ውጤት ለማምጣት ሙሉ በሙሉ ቁርጠኛ መሆኗን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አረጋገጡ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ኢትዮጵያ ኮፕ 32ን እንድታስተናግድ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ትልቅ ኃላፊነት ስለሰጠን ክብር ይሰማናል ብለዋል።

አፍሪካ በ2025 በተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ኮንፈረንስ (COP 30) ላይ በብራዚል በአንድ ድምጽ ተናግራለች፤ ዓለምም አዳምጧል ብለዋል።

እንዲሁም ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ በ2027 በአዲስ አበባ COP 32ን ለማስተናገድ ያቀረበችውን ጥያቄ ሙሉ በሙሉ ለደገፉ የአፍሪካ ሀገራት ተወካዮች ምሥጋና አቅርበዋል።

በሰው ልጆች ኑሮ በጣም አንገብጋቢ ከሆኑት ተግዳሮቶች መካከል አንዱን ለመቅረፍ እንዲቻል የጋራ ጥረቶችን ለመምራት ዕድሉን ስላገኘንም አመሥጋኞች ነን ብለዋል።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይህን ትልቅ ኃላፊነት ስለሰጠንም ክብር ይሰማናል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ይህ ዕውቅና ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ላይ ያላትን ቁርጠኛ ርምጃ፣ አመራር ብሎም ዋና ዋና ዓለም አቀፍ ዝግጅቶችን የማስተናገድ የዳበረ ዐቅም ያሳያል ሲሉም በአጽንኦት ገልጸዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ በምታስተናግደው የኮፕ 32 መድረክ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የጋራ ርምጃን የሚያበረታታ ጠንካራ እና ትርጉም ያለው ውጤት ለማምጣት ሙሉ በሙሉ ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም