የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እንግዶቹን መቀበል የሚያስችል የተሟላ ዝግጅት አድርጓል - ምክር ቤቱ - ኢዜአ አማርኛ
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እንግዶቹን መቀበል የሚያስችል የተሟላ ዝግጅት አድርጓል - ምክር ቤቱ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 5/2018(ኢዜአ)፦ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል 20ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ለማክበር የሚመጡ እንግዶቹን ለመቀበል የተሟላ ዝግጅት ማድረጉን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ዛህራ ሁመድ ገለጹ።
ምክትል አፈ ጉባኤዋ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በአጭር ጊዜ በዓሉን ለማስተናገድ ያከናወነው ቅድመ ዝግጅት የሚደነቅ ነው።
እንደ ክልል አብዛኛዎቹ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን አንስተው፤ ቀሪ ስራዎችን በቀሩት ጊዜያት እንዲጠናቀቁ አቅጣጫ መቀመጡን ተናግረዋል።
በዓሉን የክልሉን ሁለንተናዊ አቅሞች ለማስተዋወቅ መጠቀም ይገባል ሲሉም ምክትል አፈ ጉባኤዋ አሳስበዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት የጽህፈት ቤት ሀላፊ ትግሉ መለሰ በበኩላቸው፤ ክልሉ በአጭር ጊዜ የመሰረተ ልማት ክፍተቶችን ለማሟላት ያደረገው ዝግጅት ሰፊና የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።
በዓሉን በሚመጥን መልኩ የተገነቡ የመንገድ፣ የስቴዲየም፣ የሆቴሎችና የሁነት ማሳያ ፕሮጀክቶች መሰረተ ልማቶችን በአጭር ጊዜ በጥራት ሰርቶ ማጠናቀቅ እንደሚቻል ተሞክሮ የሚወሰድበት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ክልሉ ቀኑን በድምቀት ማስተናገድ የሚያስችል በቂና የተሟላ ዝግጅት ማድረጉን መመልከታቸውን የጽህፈት ቤት ሀላፊው አስታውቀዋል።