ቀጥታ፡

በጥምር ግብርና ስኬት ያስመዘገቡት አርሶ አደር ወልዴ አርጋኒ

(በእንዳልካቸው ደሳለኝ - ከወልቂጤ ኢዜአ ቅርንጫፍ)

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ ዞን ምሁር አክሊል ወረዳ ጨዛ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። ለዘመናት ባከናወኑት የግብርና ልማት ሥራ ኑሯቸው ከእጅ ወደ አፍ የዘለለ አልነበረም። ዛሬ ላይ ሆነው ያን ዘመንና ያሳለፉትን ዕድሜ ሲያስታውሱ ይቆጫሉ። በኋላ ቀር መንገድ ሲያከናውኑት ከነበረው የግብርና ልማት ሥራቸው ተጠቃሚ መሆንም፤ ሀብት ማፍራትም ሳይችሉ ቀርተዋል።


 

አርሶ አደር ወልዴ አርጋኒ ይባላሉ። ከሰበሰቡት ሰብል ጎተራቸው ሳይጎድል፣ ከእንስሳት እርባታ ስራቸውም ጥገታቸው ሳትነጥፍ ማየት የዘውትር ህልማቸው ነበር።

ለም መሬት ይዘው ምርታማ ባለመሆናቸው ሲቸገሩ፣ የሚሰራ ጉልበት ይዘው ማዕዳቸው እየጎደለ የጎልማሳነት ዕድሜ መባቻ ድረስ ችግር ሲፈራረቅባቸው ዓመታትን አሳልፈዋል።

ይህ ፍላጎታቸው ሰምሮ፣ ጓሯቸው ለምቶ፣ ቤታቸው ሞልቶና ጥሪት አፍርተው የማየት ውጥናቸው ሳይሳካ ዓመታት ቢቆጠሩም ዛሬ ግን በጀመሩት የጥምር ግብርና ሥራ ነገሮች ተቀይረዋል። የዓመታት ምኞታቸውን ማሳካት ጀምረዋል። ከስድስት ዓመታት በፊት በትንሽ መሬት ላይ የጀመሩት የጥምር ግብርና ሥራ ለስኬት እንዲበቁ ከማድረግ ባለፈ በአካባቢያቸው አርአያ የሆኑ አርሶ አደር አድርጓቸዋል።

የጥምር ግብርና ስራቸው ለዓመታት ከነበሩበት ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ በማውጣት ለአፍም ለኪስም ሆኗቸዋል። የመንግስት የልማት ትኩረት የሆነው ጥምር ግብርና በውስን መሬት ላይ የተለያዩ የግብርና ምርቶችን በቅንጅት እንዲያለሙ እድል ፍጥሮላቸዋል። በዋናነት በሰብል፣ በእንሰት፣ በፍራፍሬና በእንስሳት እርባታ ላይ አተኩረው እየሰሩ ይገኛሉ። ይህም የአንዱ ክፍተት በሌላው እየተሞለ ውጤታማ ስላደረጋቸው የምግብ ዋስትናቸውን ከማረጋገጥ ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን እያሳደጉ ነው።

ለቤት ፍጆታ ብቻ ያመርቱ የነበረው የእንሰት ምርትን በማስፋፋት ችግኙንና ተረፈ ምርቱን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ጭምር ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ ሆነዋል። የግብርና ግብዓቶችንና ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ተጠቅመው በሚያመርቱት ገብስ ለሌሎች አርሶ አደሮች ምሳሌ መሆን ችለዋል።


 

ዝርያቸው የተሻሻሉ ላሞችን ስለሚያረቡም ወተት ከማጀታቸው አይጠፋም። በጓሯቸው የሚያለሙትን አትክልትና ፍራፍሬ ከቤት ውስጥ ፍጆታ ባለፈ ለገበያ ማቅረብ የሚያስችል አቅም ፈጥረዋል። አርሶ አደሩ ከንብ ማነብ ሥራቸውም እንዲሁ ተጠቃሚነታቸው እያደገ ነው።

ከአካባቢው ስነምህዳር ምክንያት ብዙም ያልተለመደውን ቡና በመትከል ለፍሬ አብቅተዋል። የእሳቸውን ፈለግ የተከተሉ ሌሎች አርሶ አደሮችም ቡና ማልማት ጀምረዋል። በእጅ ያለን ሀብት ወደ ውጤት ለመቀየር ተግቶ መስራትና ጽናት ያስፈለጋል ያሉት አርሶ አደር ወልዴ፣ በግብርና ባለሙያዎች የተደረገላቸው ሙያዊ ድጋፍና የተፈጠረላቸው የገበያ ትስስር ለውጤታቸው ሚና እንዳለው ገልጸዋል። የእርሻ ልማትና የእንስሳት እርባታውን በቅንጅት ማከናወናቸውም እንዲሁ።

አርሶ አደር ወልዴ የዓመታት ቁጭታቸው ዛሬ መፍትሄ እያገኘ ነው። የጥምር ግብርና ሥራቸው በምግብ ራሳቸውን እንዲችሉና ልጆቻቸውን በጥሩ ሁኔታ እንዲያሳድጉ አስችሏቸዋል። መኖሪያ ቤትን ጨምሮ የተለያየ ሀብት ለማፍራት ምክንያት በመሆኑም ልማቱን አስፋፍቶ ለማከናወን አቅደዋል።


 

አርሶ አደር ወልዴ አርጋኒ ለአካባቢው አርሶ አደሮች ጭምር አርአያ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የጉመር ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ሙራዱ ብሩ ናቸው። ቀደም ሲል በገብስ ምርት ላይ ብቻ አተኩረው ይሰሩ የነበረውን የግብርና ሥራ እንዲቀይሩ ምክንያት እንደሆኗቸው ይገልጻሉ። ከአርሶ አደር ወልዴ በወሰዱት ልምድ ወደ ጥምር ግብርና ገብተዋል። በዚህም ድርቅ የመቋቋም አቅም ያለውን እንሰት በማሳቸው በስፋት ማልማት ጀምረዋል።

የነበሯቸውን ሀገረሰብ የዳልጋ ከብቶች በተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያዎች በመቀየር የተሻለ ተጠቃሚ ለመሆን ተግተው እየሰሩ ነው። ጥምር ግብርና የተሻለ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ከአርሶ አደር ወልዴ ተምሪያለሁ ይላሉ። ከኢኮኖሚ ጠቀሜታው ባለፈ የመሬት ለምነትን ለማስጠበቅም ጠቀሜታው የጎላ በመሆኑ የጀመርነውን ሥራ እናጠናክራለን ሲሉም ነው የገለጹት።


 

የሙህር አክሊል ወረዳ ግብርና ፅህፈት ቤት ሀላፊ መኑር ጀማል በበኩላቸው "አርሶ አደር ወልዴ አርጋኒ በውስን መሬት ገብስ፣ እንሰት፣ ቡና እና የተለያዩ ፍራፍሬዎችን በጥምር በማልማት የራሳቸውን ህይወት ከመቀየር ባለፈ ለሌሎች አርሶ አደሮች አርአያ እየሆኑን ነው ብለዋል።

አርሶ አደሩ በሽታ መቋቋም የሚችሉና ለመድሃኒትነት የሚፈለጉ የእንሰት ዝርያዎችን በማፍላት ለገበያ እያቀረቡ ይገኛሉ። ከዚህም ባለፈ በመጥፋት ላይ የነበሩ የእንሰት ዝርያዎችን የመታደግና የአፈር ለምነት እንዲጠበቅ ጉልህ ሚና ማበርከታቸውንም ተናግረዋል፡፡

የጥምር ግብርና አሰራር የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባሻገር ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ስነ-ምህዳራዊ ጥቅሞችን የሚያስገኝ በመሆኑ በወረዳው ትኩረት ተሰጥቶት እየተከናወነ መሆኑን ነው የገለጹት።

የአርሶ አደር ወልዴ ልምድን በማስፋት የሌሎች አርሶ አደሮችም ጓዳ ሞልቶ እንዲትረፈረፍ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው በተለይ በጥምር ግብርና አርሶ አደሩ ከራሱ ባለፈ ለሌሎች ጭምር እንዲተርፍ የማድርጉ ሥራ ይጠናከራል ብለዋል።


 

ልማቱ እርስ በእርስ የሚደጋገፉና በአንድ መሬት ላይ የተለያዩ ምርቶችን በማግኘት የተሻለ ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው። ግብርናን ለማዘመንና ምርታማነትን ለማሳደግ በሚሰራው ሥራ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች ውስጥ በጥቂት መሬት ብዙ ማምረት መቻል ነው። በመሆኑም በተለይ የመሬት እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች ለዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ጠቀሜታው የጎላ ነው።

በሥራ ውጤታማ ለመሆን ሁሉም ነገር ምቹና አልጋ በአልጋ መሆን የግድ እንዳልሆነ አርሶ አደሩ ጥሩ ማሳያ ናቸው። ወጣቶች በአካባቢያቸው ያለውን ዕድል እንዴት ወደሀብትነት መቀየር እችላለሁ ብለው ከሰሩ ውጤታማ እንደሚሆኑ የእሳቸው የስኬት ጉዞ በቂ ማሳያ ነው። ሰርቶ ለመለወጥም ሆነ ሀብት ለማፍራት ችግሮችን በጽናት ማለፍ እና የሥራ ትጋት ወሳኝ ነውና ተሞክሯቸውን ማስፋት ያስፈልጋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም