ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል አማራጭ የሌለው መንገድ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል አማራጭ የሌለው መንገድ ነው
አዲስ አበባ፤ሕዳር 5/2018 (ኢዜአ)፡-በኢትዮጵያ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት የሚያስገኝና አገርን ወደፊት የሚያራምድ አማራጭ የሌለው መንገድ ነው ሲሉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።
በሃይል አማራጭ ስልጣን ለመቆጣጠር የሚደረግ ትግል በየትኛውም የሕግ ማዕቀፍ ተቀባይነት የሌለውና በወንጀል የሚያስጠይቅ መሆኑ ይነገራል።
በኢትዮጵያ የቀደመ ታሪክ ስልጣንንም ሆነ የፖለቲካ ፍላጎትን በዴሞክራሲያዊ መንገድ በውይይት ከመፍታት ይልቅ በሃይል አማራጭ ለማስፈጸም አዝማሚያዎች በተደጋጋሚ እንደሚታዩ የታሪክ ሰነዶች ያሳያሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመደመር መንግሥት መጽሐፋቸው ገፅ 328 ላይ የኃይል ፍላጎት ካልተገራ ሁሉን መጠቅለል እንደሚፈልግ ያነሳሉ።
ይሄም በፖለቲካ ገበያው ላይ ትርምስ ይፈጥራል። የኃይል ፍሰትና ስበትም ይረበሻል። ትርምሱ ሥርዓትን ይበጠብጣል። በዚህም የኃይል ሞገዱ ማንን እንደሚያጠፋ መለየት እስኪያዳግት ድረስ ረብሻ እንደሚሆን አንስተዋል።
በመደመር መንግሥት መጽሐፍ ገፅ 383 ላይ እንደተመላከተው፤ አሁን ባለችው ኢትዮጵያ የሀሳብ ገበያ ባህል እንዲሆን እየተሰራ ነው።
ለዚህም መንግስት ሶስት መንገዶችን እየተከተለ ይገኛል። እነዚህም ሀገራዊ ምክክር፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምክክርና የሕዝብ መድረኮች ናቸው።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ለህዝብ ጥቅምና ለአገር ዕድገት እንታገላለን የሚል አቋም ያለው ማንኛውም ቡድን ዓላማውን በሰላማዊ መንገድ ከማሳካት ውጪ አማራጭ የለውም ይላሉ።
በተለይም መንግስት ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግል በሩን ክፍት ባደረገበት ወቅት ከሰላማዊ ትግል ውጭ ምንም አማራጭ እንደሌለ ያነሳሉ።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ከፍተኛ አመራር ቀጄላ መርዳሳ እንደሚሉት፤ መንግስት በሃይል አማራጭ ፍላጎታቸውን ለማሳካት የሚፈልጉ ቡድኖችን ወደ ሰላም መጥተው በጋራ እንዲሰሩ በተደጋጋሚ ጥሪ እያቀረበ ነው።
ይህን ጥሪ ተቀብለው የመጡ በርካታ ሃይሎች ቢሆኑም አሁንም ድረስ የሰላም አማራጭን በመተው ወደ ኋላ የሸሹ መኖራቸውን አንስተዋል።
የህብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አበራ በቀለ፣ በኢትዮጵያ በሃይል ፍላጎትን ለማሳካት መሞከር ጊዜው አልፎበታል ይላሉ።
ማንም ቡድን ወይም ፖለቲካ ፓርቲ የሚፈልገውን የፖለቲካ ዓላማ ለማሳካት ከሰላም ውጪ ያለው አማራጭ ተቀባይነት የሌለው ነው ብለዋል።
የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የውጭና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ሃላፊ መብራቱ ዓለሙ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የአገርን ሰላም ማረጋገጥ ለአንድ አካል የሚተው አለመሆኑን ያነሳሉ።
የታጠቁ ሃይሎች አለን የሚሉትን ጥያቄ ወደ ውይይት እንዲያመጡ ተደጋጋሚ ጥሪ እየቀረበ መሆኑን አመልክተው፤ ለዚህም አገራዊ ምክክርን የመሰሉ አማራጮች መቅረባቸውን አንስተዋል።
እንደ ተፎካካሪ ፓርቲዎቹ ገለጻ፤ የሰላማዊ ትግል አንዱ ዓላማ ለህዝብና ለአገር የሚጠቅሙ አጀንዳዎቸን መቅረጽና በሀሳብ ልዕልና መንግስት እንዲቀበለው ማስገደድ ነው።
በአንዳንድ አካባቢዎች ፍላጎታቸውን በሃይል ለማሳካት የታጠቁ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ሆነ ሌሎች ቡድኖች ወደ ሰላማዊ ትግል እንዲመለሱም ጥሪ አቅርበዋል።