በፖለቲካው ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶች ኢትዮጵያን ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋገሩ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በፖለቲካው ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶች ኢትዮጵያን ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋገሩ ናቸው
አዲስ አበባ፤ሕዳር 5/2018 (ኢዜአ)፡-በፖለቲካው ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶች ኢትዮጵያን ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋገሩ መሆናቸውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጂጌ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
በኢትዮጵያ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በሁሉም መስከ የተመዘገቡ ስኬቶች ኢትዮጵያን የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ የተጀመረው ጉዞ ማሳያ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጂጌ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በፖለቲካው ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶች ኢትዮጵያን ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋገሩ ናቸው፡፡
የጠላትና ወዳጅ ሆኖ የቆየው የፖለቲካ ሂደትን ለመቀየር ታሪካዊ እርምጃዎች መወሰዳቸወን ተናግረዋል።
በፖለቲካው መስክ የነበረውን አግላይነት በማስቀረት ሁሉንም አሳታፊ በማድረግ እየተከናወኑ ያሉ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ስራዎች መኖራቸውንም ገልጸዋል፡፡
ለአብነትም 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በኃላ በመንግስት ምስረታ ሂደት ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አባላት በካቢኔ ውስጥ በማሳተፍ ለሀገር ዕድገት በጋራ እንዲሰሩ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
ይህም በሀገር ደረጃ የመግባባት ዲሞክራሲን ለመገንባት የተጀመረው ሂደት በተግባር የተገለጸበት መሆኑን ጠቁመው፤ የተለያዩ አመለካከቶች የያዙ የኢትዮጵያ ልጆች በሀገራዊ ጉዳዮች በጋራ መስራት እንደሚችሉም ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
ይህ ሂደትም ኢትዮጵያዊ መልክ ያለውና ኢትዮጵያዊ መግባባት ላይ የተመሰረተ ዲሞክራሲ ለመገንባት የተጀመረው ጥረት አካል መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በኢትዮጵያ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ታስቦ የተቋቋመው ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በፖለቲካው ዘርፍ እየተገኙ ከሚገኙ ስኬቶች መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ብቻ ለመፍታት አቅጣጫ በማስቀመጥ ተግባራዊ በመደረግ ላይ መሆኑም ሌላኛው በፖለቲካ ዘርፍ ያለ ስኬት መሆኑን ጠቁመው የፕሪቶሪያው ስምምነትንም ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡
ትጥቅ ያነገቡ ቡድኖች ሰላማዊ ፖለቲካን እንዲያራምዱ በሩ ክፍት መደረጉም የፖለቲካ ባህል እየተቀየረ ለመሆኑ ሌላኛው ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተጀመረው የመንግስት ጥረት ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡
ለአብነትም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላ፣ በሶማሌና በሌሎችም ክልሎች የነበሩ ችግሮችን ሙሉ በሙሉ በመፍታት በክልሎቹ ሰላማዊ የልማት እንቅስቃሴ እንዲካሄድ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ከበርካታ የታጠቁ አካላት ጋር በመነጋገር ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመጡ መደረጉን ጠቁመው፤ በአማራ ክልልም የሰላም በር ተከፍቶ ችግሮችን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በለውጡ ሂደት በሁሉም መስክ የተመዘገቡ ውጤቶችን ለማስቀጠል መንግስት በላቀ ብቃትና ቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡