ቀጥታ፡

አለመግባባቶችን በዘላቂነት ለመፍታት በሚካሄደው ምክክር የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና ወሳኝ ነው

አዳማ ፤ ሕዳር 5/2018(ኢዜአ)፦ ልዩነቶችንና አለመግባባቶችን በዘላቂነት ለመፍታት እየተካሄደ ባለው የምክክር ሂደት የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና ወሳኝ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገለፁ።

ኮሚሽኑ የምክክር ሂደቱን የተሳካ ለማድረግ በማለም የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሳተፉበት የምክክር መድረክ በአዳማ በማካሄድ ላይ ነው።


 

ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በመድረኩ እንዳሉት፤ ኮሚሽኑ የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራዎችን በማገባደድ ወደ ቀጣይ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ለመሻገር በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።

በዚህም ህብረተሰቡ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ምሁራን፣ ማህበራትና ተቋማት፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በምክክሩና በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ በንቃት መሳተፋቸውን ገልጸዋል።

የምክክር ሂደቱን የተሳካ በማድረግ ወደ ቀጣይ ሀገራዊ ጉባኤ ለማሸጋገር ኮሚሽኑ አጀንዳ የማሰባሰብና የመቅረፅ ስራ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል ።

ሀገራዊ ምክክሩ አሳታፊና አካታች እንዲሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ ወሳኝ ነው ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ ከ80 በመቶ በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ባለቤት ሆነው በንቃት እየተሳተፉ ይገኛሉም ብለዋል።

ልዩነቶችንና አለመግባባቶችን በዘላቂነት ለመፍታት እየተካሄደ ባለው የምክክር ሂደት የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚኖራቸው ሚና ወሳኝ መሆኑንም አስረድተዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች እስካሁን በተካሄደው የምክክር ሂደት ንቁ ተሳትፎ እንደነበራቸው ገልፀው መድረኩ የፓርቲዎቹን የእስከ አሁን ተሳትፎና ሚናቸውን በቀጣይ ይበልጥ እንዲያሳድጉ በማለም መዘጋጀቱን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን አየለ በበኩላቸው፥ ምክክሩ የተሳካ የፖለቲካ ሽግግርን ለማካሄድና ልዩነቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል።


 

በሀገሪቷ ለቆዩ አለመግባባቶች መፍትሄ ለመሻት፣ መተማመንና አዲስ የፖለቲካ እሳቤን ለመፍጠር ምክክሩ ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑንም ተናግረዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤቱ ሁሉን አካታችና አሳታፊ ሀገራዊ ምክክር እንዲካሄድ ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰው፥ በዚህም ሃሳብ ከማመንጨት ጀምሮ ግልጽና ገለልተኛ አካል እንዲመራው የድርሻውን መወጣቱን አስረድተዋል።

በተጨማሪም የጋራ ምክር ቤቱ አባል የፖለቲካ ፓርቲዎች በምክክሩ ዓላማና ሂደት ላይ የተሻለና ግልጽ ግንዛቤ እንዲኖራቸው በማድረግ ረገድ አስተዋፅኦ ማድረጉንም ገልጸዋል።

ምክር ቤቱ የሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች አጀንዳ በማሰባሰብና በማደራጀት ለኮሚሽኑ የተጠቃለለ አጀንዳ ማስረከቡን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም