ለሀገራዊ ፕሮጀክቶች ስኬት የሚጠበቅብንን ድጋፍ እናደርጋለን - ኢዜአ አማርኛ
ለሀገራዊ ፕሮጀክቶች ስኬት የሚጠበቅብንን ድጋፍ እናደርጋለን
ወልቂጤ ፤ሕዳር 5/2018 (ኢዜአ)፡- ሀገራዊ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን የጋራ ጥቅም የሚያረጋግጡና ከተረጂነት ለመላቀቅ የሚያስችሉ በመሆናቸው ያለ ልዩነት ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክርቤት አባላት ገለጹ።
በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ምረቃ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቀጣይ የሚገነቡ አዳዲስ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
የማዳበሪያ ፋብሪካ፣ የነዳጅ ማጣሪያ፣ የቤቶች ግንባታ፣ የዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታና ሌሎችም ከፕሮጀክቶቹ መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
ፕሮጀክቶቹ የሀገሪቱን ብልጽግና በማረጋገጥ ከድህነት ለመውጣት ያላቸው ፋይዳ ላቅ ያለ በመሆኑ ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ የመላው ኢትዮጵያውያን ድጋፍና ርብርብ ወሳኝ መሆኑ ይታመናል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የፖለቲካ ፖርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ፤ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን የጋራ ጥቅም የሚያረጋግጡና ከተረጂነት ለመላቀቅ የሚያስችሉ በመሆናቸው ስኬታማ እንዲሆኑ ያለ ልዩነት ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ደምስ ገብሬ እንዳሉት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ዳር ድንበር ማስከበር የሁሉም ዜጋ ሃላፊነት ነው።
ልማት እና ሰላምን ማረጋገጥ የሚቻለው የግዛት አንድነትን በማስጠበቅ፣ የዜጎችን ተጠቃሚነትና የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ይፋ የተደረጉ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እንዲያንሰራራ ከማድረግ ባለፈ ከቀጣናው ሀገራት ጋር በጋራ ለማደግ ወሳኝ በመሆናቸው አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል።
ከለውጡ ወዲህ ሀገራዊ ሀብትን ለህዝብ ጥቅም ማዋል የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ያሉት ደግሞ የምክር ቤቱ አባል ሔኖክ አብዱልሰመድ ናቸው።
ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያን ከቀጣናው ሀገራት ጋር በኤሌክትሪክ ኃይልና በመሰረተ ልማት በማስተሳሰር በትብብር ለመስራት ትልቅ አበርክቶ ይኖረዋል ብለዋል፡፡
የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት ውል መገባቱ ይወጣ የነበረን የውጭ ምንዛሬ ለማስቀረትና የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ጉልህ ሚና እንዳለውም ገልጸዋል፡፡
እነዚህ ሃገራዊ ፕሮጀክቶች ለሀገር ኢኮኖሚያዊ ትራንስፎርሜሽን ካላቸው ጠቀሜታ ባሻገር ዜጎች በየተሰማሩበት የስራ መስክ ለሚያደርጉት ጥረት ጉልህ ሚና ስለሚኖራቸው ተገቢውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ሌላው የምክር ቤቱ አባል አቶ እንዳለ ኤርግዶ ፕሮጀክቶቹ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ይበልጥ በማሳደግ የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማላቅ ቀላል የማይባል አበርክቶ አላቸው ብለዋል።
ተመርቆ ስራ ላይ መዋል የጀመረው የጋዝ ፋብሪካ ኢትዮጵያ ተፈጥሮአዊ ሃብቶቿን በራሷ አቅም ማልማት እንደምትችል ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል።
የማዳበሪያ ፋብሪካ በሃገር ውስጥ መገንባት ከሌሎች ሃገራት ከጥገኝነት በመላቀቅ በግብርናው ዘርፍ እመርታዊ ለውጥ ለማምጣት ወሳኝ ድርሻ ስላለው ለፕሮጀክቶቹ ስኬት ከምንጊዜውም በላይ በትብብር እንሰራለን ብለዋል።