ቀጥታ፡

የሊጉ መሪ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከሃዋሳ ከተማ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል 

አዲስ አበባ፤ ህዳር 5/2018(ኢዜአ)፦  በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የስድስተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ሁለት ጨዋታዎች በአበባ ቢቂላ ስታዲየም ይካሄዳሉ።

ከቀኑ 7 ሰዓት ሃዋሳ ከተማ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ይጫወታሉ።

ሃዋሳ ከተማ በሊጉ ባደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች አራት ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፏል። 

በጨዋታዎቹ ዘጠኝ ግቦችን ሲያስቆጥር ሶስት ግቦችን አስተናግዷል። ቡድኑ በ12 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ተጋጣሚው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በበኩሉ በሊጉ ያከናወናቸውን አምስት ጨዋታዎች አሸንፏል። 13 ግቦችን ሲያስቆጥር የተቆጠረበት አንድ ግብ ብቻ ነው።

ቡድኑ በ15 ነጥብ ሊጉን እየመራ ይገኛል።

በዘንድሮው የውድድር ዓመት ጥሩ ጅማሮ ያሳዩት ሁለቱ ክለቦች በጨዋታው ተመጣጣኝ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በሌላኛው መርሃ ግብር ሲዳማ ቡና ከአዲስ አበባ ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። 

ሲዳማ ቡና በሊጉ ካደረጋቸው አራት ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ ሶስት ጊዜ አቻ ወጥቷል። 

በጨዋታዎቹ ሲዳማ ቡና አምስት ግቦችን ሲያስቆጥር ሶስት ግቦችን አስተናግዷል። ቡድኑ በስድስት ነጥብ ስድስተኛ ደረጃን ይዟል። 

ተጋጣሚው አዲስ አበባ ከተማ በሊጉ ካደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች መካከል አንዱን ሲያሸንፍ አራት ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። 

በጨዋታዎቹ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር 11 ጎሎች ተቆጥረውበታል። ቡድኑ በሶስት ነጥብ 13ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። 

ጨዋታው ሁለቱ ቡድኖች ወደ አሸናፊነት መንገድ ለመመለስ የሚያደርጉት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም