የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን አንድነትን ከማጎልበት ባለፈ ለቱሪዝሙ ዘርፍ ዕድገት ሚናው የጎላ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን አንድነትን ከማጎልበት ባለፈ ለቱሪዝሙ ዘርፍ ዕድገት ሚናው የጎላ ነው
አዲስ አበባ፤ሕዳር 5/2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን እንደ ሀገር ወንድማማችነትንና እህትማማችነትን ከማጠናከር ባለፈ ለቱሪዝም ዘርፍ የጎላ ፋይዳ እንዳለው ተመላከተ።
20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን “ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለኅብረ-ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሐሳብ ሕዳር 29 ቀን 2018 ዓ.ም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ ይከበራል።
ይህን አስመልክቶ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሳሙኤል መንገሻ ለኢዜአ እንዳሉት፥የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በክልሉ መከበሩ ዘርፈ-ብዙ ጥቅም አለው።
ክልሉ ያለውን ፀጋ ለማስተዋወቅ ከመላው ኢትዮጵያ የሚመጡ እንግዶችን መቀበል እና ይህን ታላቅ ቀን ማስተናገድ ጥቅሙ ብዙ ነው ብለዋል።
በተለይም ከቱሪዝም ዘርፍ አንጻር በክልሉ የሚገኙ ባህሎችን እና በርካታ መስኅቦችን ለማስተዋወቅ የጎላ ፋይዳ እንዳለው አስገንዝበዋል።
እንዲሁም የእርስ በርስ ግንኙነትን ከማጠናከር ባለፈ የሥራ ዕድሎችን እና የዘርፉን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንደሚያሳድገው አስረድተዋል።
ለዚህም በድምቀት ለማስተናገድ የሚያስችሉ ዝግጅቶች መደረጋቸውን እና አሁንም ተጠናክረው መቀጠላቸውን አረጋግጠዋል።
19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን “ሀገራዊ መግባባት ለኅብረ-ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሐሳብ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አስተናጋጅነት በአርባምንጭ ከተማ መከበሩ ይታወሳል።