የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀንን ለማክበር እየተደረገ ያለው ዝግጅት በጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል-አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር - ኢዜአ አማርኛ
የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀንን ለማክበር እየተደረገ ያለው ዝግጅት በጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል-አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር
አዲስ አበባ፤ሕዳር 4/2018 (ኢዜአ)፡-20ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ለማክበር የሚደረገው ዝግጅት በሁለንተናዊ መልኩ በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ገለፁ።
20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ''ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለኀብረ ብሔራዊ አንድነት'' በሚል መሪ ሀሳብ በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ ይከበራል።
20ኛው የብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን የኢትዮጵያን ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትን በሚያጠናክሩ ተግባራት እንደሚከበርም ከምክር ቤቱ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
ሀገራዊ መግባባት እንዲፈጠር፣ ህብረ ብሔራዊነት እንዲጎለብትና ፌዴራላዊ አስተሳሰብ እና እሴቶች እንዲያድጉ የሚያደርጉ ስራዎች እንደሚከናወኑ ነው የተመለከተው።
ዛሬ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሆሳዕና ከተማ በሀገር አቀፍ ደረጃ ህዳር 29 ለሚከበረው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን የመሰረተ ልማት ስራዎች አፈፃፀም ያለበት ሂደት ተጎብኝቷል፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻዉ ጣሰዉ (ዶ/ር)ን ጨምሮ የክልሉ እና የፌዴራል ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
በጉብኝቱ በዓሉን ለማክበር የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል በሆሳዕና ከተማ እየተደረገ ያለ ዝግጅት፣ 20ኛው የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች በዓል የሚከበርበት የአቢዮ ኤርሳሞ መታሰቢያ ስታዲየም ግንባታ ያለበት ደረጃ፣ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ፅህፈት ቤት ግንባታ እና ሌሎች የልማት ስራዎችን ተመልክተዋል፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በዚሁ ወቅት፥ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል 20ኛው የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀንን ለማስተናገድ እያደረገ ያለው ዝግጅት በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አንስተዋል።
በዓሉን ኢትዮጵያን በሚመጥን መልኩ ለማክበር በቀሩት ጥቂት ቀናት ስራዎችን ለማጠናቀቅ የሚደረገው ርብርብ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አመልክተዋል።
የማዕከላዊ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ በዓሉን በሆሳዕና ከተማ በደመቀ ሁኔታ ለማክበር በቂ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
ቀኑ የኢትዮጵያዊያን ወንድማማችነትና እህትማማችነትን በሚያጠናክር መልኩ እንደሚከበር ጠቁመው፤ ቀኑን ለማክበር የሚመጡ እንግዶችን በፍቅር ተቀብሎ ለማስተናገድ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።
ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ሲከበር ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ትሩፋቶች እንደተገኙበት ይታወሳል።